ምርጫ፣ ሰላም እና ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፡፡

20

 

ደሴ: መጋቢት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኅላፊዎች በደቡብ ወሎ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራዎችን የሚገመግም የውይይት መድረክ በደሴ ከተማ አካሂደዋል።

ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ በኾነ መንገድ እንዲከናወን ሥራዎች በየደረጃው በሚገኙ የመንግሥት እና የግል አደረጃጀቶች አማካኝነት እየተሠሩ መኾናቸው ተገልጿል።

የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ መሪዎችም ከክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጋር በምርጫ ዝግጅት ሂደት፣ በልማት ሥራዎች እና በጸጥታ ኹኔታዎች ላይ ባከናወኗቸው ሥራዎች ላይ በደሴ ከተማ ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ በምርጫው ሂደት እና በጸጥታ ሥራ ላይ የተከናወኑ የሥራ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ ዳኘው ገለጻ አድርገዋል። ዞኑ በእስካሁኑ የሥራ እንቅስቃሴ የተሻለ የፈፀመ መኾኑንም አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጅ የፖለቲካ ተደራሽነት፤ የደኅንነት፤ የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ሥራዎች ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣይ ጠንካራ ሥራዎችን በማከናወን ሰላማዊ፣ ተዓማኒ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ እንሠራለን ነው ያሉት።

ወረዳዎችን በመደገፍ ከማኀበረሰቡ ጋር በቅርበት መሥራት እና የተለያዩ መድረኮችን መፍጠር መቻላቸውም ተመላክቷል። ጉድለቶችን በመለየት ሕዝቡ ነጻ እና ገለልተኛ ምርጫ እንዲያደርግ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ መኾኑንም አስታውቀዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፤ የብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) እና የሌሎች የልማት ሥራዎች በጥሩ ኹኔታ እየተከናወኑ መኾኑንም አንስተዋል።

የውይይት መድረኩን የመሩት በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ ደቡብ ወሎ ዞን በክልሉም ኾነ በፌዴራሉ መንግሥት ምሥረታ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን በመገንዘብ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዞኑ በጠራ ዕይታ ላይ የተመሠረተ መሪ ያለው በመኾኑ የተሻለ የልማት እና የሰላም እንቅስቃሴ እንዲኖረው አስችሏል ያሉት አቶ ፍሰሃ “ምርጫ ሰላም እና ልማት ተያያዥነት ያላቸው በመኾኑ በትልቁ አልመን ልንሠራ ይገባል” ብለዋል። በውይይቱ የተነሱ ክፍተቶችን በመሙላትም የተጀመሩ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፡-መሐመድ በቀለ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን አስመረቀ፡፡
Next article“የአባት ክትትልና የልጅ ጥረት ያፈራው ድንቅ ውጤት”