
ባሕር ዳር: መጋቢት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት የጤና ፖሊሲን በማሻሻል ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር አልም ከሚሠራቸው ተግባራት መካካል ጥራቱን የጠበቀ የጤና ተቋም መገንባት እና ተደራሽ ማድረግ ዋናው ነው።
የአማራ ክልልም ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ተቋማት እየገነባ ይገኛል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ እየገነባቸው ከሚገኙ የጤና ተቋማት መካከል በምሥራቅ ጎጃም ዞን በደባይ ጥላት ግን ወረዳ በሁለት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ በ2010 ዓ.ም የተጀመረው የቁይ የመጀመረያ ደረጃ ሆስፒታል አንዱ ነው።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የጤና መሠረተ ልማት ዳይሬክተር ደርባባው ሽፈራው ሆስፒታሉ በ2010 ዓ.ም በክልሉ መንግሥት ከ297 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት የግንባታ ሥራው መጀመሩን አስታውሰዋል። ይሁን እንጅ በቁሳቁስ ዋጋ ንረት ምክንያት ተቋርጦ መቆየቱን ተናግረዋል።
ግንባታው እንደገና ከሴኔ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባሩ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። አሁን ላይ የግንባታ ሥራው 95 ነጥብ 5 በመቶ አፈጻጸም መድረሱንም ተናግረዋል። በቀጣይ ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ርክክብ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል። በተያዘው በጀት ዓመት ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ በትኩረት ይከናወናል ነው ያሉት።
ሆስፒታሉ ተጠናቅቆ ሥራ ሲጀምር ከ100 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
ተቋሙ የማኅበረሰቡን የረጅም ጊዜ የልማት ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል። ፍትሐዊ የጤና ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
አሁን ላይ ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው በመቅደላ ኮንስትራክሽን የኘሮጀክቱ ሥራ አሥኪያጅ ባዬ ገጥአለ የቁይ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በአንድ ዓመት ለማጠናቀቅ ውል ይዘው እንደነበር ገልጸዋል። ነገር ግን ግንባታው በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ዳግም ተቋርጦ እንደነበርም አንስተዋል። ከታኅሣሥ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ግን ወቅታዊ ችግሩን በመቋቋም የግንባታ ሥራው እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ የሽዋስ አንዷለም ሆስፒታሉ የሕዝቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ኾኖ የቆዬ መኾኑን ተናግረዋል። የግንባታ ሥራው በጥራት እና በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ደጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።
ግንባታው ሲጠናቀቅ በአጎራባች ወረዳዎች እና ቀበሌዎች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በቅርበት አገልግሎት እንዲያኙ ያደረጋል ነው ያሉት። በተለይም የእናቶችን እና የሕጻናትን ጤና ለመጠበቅ ያግዛል ብለዋል።
በደባይ ጥላት ግን ወረዳ በቁይ ከተማ ነዋሪ የኾኑት ይታየው አልማው ረጅም ርቀት ወደ ሌላ ቦታ በመሄድ ሕክምና ያገኙ እንደነበር እንስተዋል። በተለይም ወላድ እናቶች ለሕክምና ሩቅ ቦታ ሲሄዱ ሕይወታቸው ከመንገድ ያልፍ እንደነበርም አስታውሰዋል። ይህን ተረድቶ መንግሥት እልባት ለመስጠት እያደረገው ላለው ጥረት አመስገነዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
