
ደብረ ማርቆስ: መጋቢት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ያሠለጠናቸውን የ13ኛ ዙር የታክቲካል ወንጀል ምርመራ የፖሊስ አባላትን በደብረ ማርቆስ ከተማ አስመርቋል።
ተመራቂ የፖሊስ አባላት በንድፈ ሀሳብ እና በተግባር ያገኙትን ዕውቀት በመጠቀም ለፍትሕ ሥርዓቱ መሻሻል የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
ሰላምን የማረጋገጥ ጉዳይ ለፖሊስ ወይም ለጸጥታ አካላት ብቻ የሚተው አይደለም ያሉት ተመራቂ የፖሊስ አባላቱ በጋራ ለሰላም መስፈን የሚጠበቅብንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ዋና መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ዳምጤ ባዬ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የታጠቀ፣ ነጻ እና ገለልተኛ የፖሊስ ተቋም ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያሳልጡ፤ በአሠራር እና በአደረጃጀት ተጨባጭ የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
የወንጀል ምርመራ ሥራ ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ መሠረት መኾኑን በመገንዘብ ሙያዊ ሥነ ምግባርን በተላበሰ እና የዜጎችን መብት ባከበረ መልኩ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ለተመራቂ የፖሊስ አባላት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ ከዋና ዋና የፖሊስ ተግባራት መካከል አንዱ የኾነው የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ዋነኛው መሣሪያ መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡
ተመራቂ የፖሊስ አባላት የወሰዱትን ሥልጠና ወደ ተግባር በመቀየር እና ተገቢውን ምርመራ በማድረግ አጥፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ እና ዜጎች ፍትሕ እንዲያገኙ በትጋት መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
