በሴቶች ላይ ጥቃት ያደረሱ አካላትን በመለየት የእርምት እርምጃ እየተወሰደ ነው።

6

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ሥርዓተ ጾታን መሠረት ያደረገ እና ጥቃትን መከላከል አላማው ያደረገ ሥልጠና በጎንደር ከተማ እየሰጠ ነው።

በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር የፍትሕ ተግባራትን ለመስጠት እና በጾታዊ ጥቃት ላይ ችግር የፈጠሩ አካላትን መርምሮ ውሳኔ ለማስተላለፍ ፈተና መኾኑ በሥልጠናው ተነስቷል።

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ወንዳቸው ሠራው ባለፉት ስድስት ወራት በሴቶች ላይ ጥቃት ያደረሱ አካላትን በመለየት የእርምት እርምጃ መሰጠቱን ገልጸዋል። ከ200 በላይ ግለሰቦች የተለያዩ የሕግ ቅጣት እንደተላለፈባቸውም ተናግረዋል።

ፍትሕን ለማስፈን እና የዜጎች በሕይወት ተረጋግተው የመኖር ሰብዓዊ መብታቸውን ለማረጋገጥ የፍትሕ ሥርዓትን ማዘመን እና አሠራሮቹን ማሻሻል እንደሚገባም ገልጸዋል።

ፍትሕ የማግኘት መብት አንዱ የሰብዓዊ መብት አካል በመኾኑ የዜጎችን መብት በመጠበቅ የፍትሕ ተቋማት ውጤታማነት እና የሕግ ጥራት ወሳኝ መኾኑን ነው የተናገሩት።

ጾታዊ ጥቃት አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ እየሰፋ መምጣቱንም ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የሰብዓዊ መብቶች ዳይሬክተር እሸቱ አለነ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችን አፋጣኝ የፍትሕ ውሳኔ እንዲያገኙ የሚያስችሉ አሠራሮችን በመዘርጋት ወደ ተግባር መግባቱን አንስተዋል።

አልፎ አልፎ የሚሰተዋሉ የፍትሕ ውሳኔ መጓተት አሁንም ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ሕክምና እና ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ እንዳያገኙ አሉታዊ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ቀኑ ቢያድጎ የሴቶች ጥቃትን ለመከላከል እስከታችው ኅብረተሰብ ክፍል ድረስ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውን ገልጸዋል። ሴቶች ላይ የሚደርግ ማንኛውም ጥቃት ሊቆም ይገባል ብለዋል።

የሴቶችን ጥቃት ለማስቆም ቅድመ መከላከል እና ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ተግባራዊ ማድረግ ላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ተገልጿል።

ዘጋቢ: አዲሱ ተስፋዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሹዋሊድ በዓል ሰላምን፣ አብሮነትን እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ ይከበራል።
Next articleየወንጀል ምርመራ ሥራ ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ መሠረት ነው።