
ደሴ: መጋቢት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው የዛሬ ተመራቂዎችን ሳይጨምር ባለፉት ጊዜያት በአምስት ዙር ከ4 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ማስመረቁ ተገልጿል። ዘንድሮም 698 ተማሪዎችን እያስመረቀ ነው።
የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ካሳ ሻውል (ዶ.ር)
ባለፉት ዓመታት በትምህርት ሂደቱ በርካታ ውጣ ውረዶችን በትጋት ተወጥታችሁ ለዛሬ የምረቃ በዓል በመድረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ጥንካሬያችሁ ነገ ወጥታችሁ ለምትቀላቀሉት ሰፊው ዓለም የሥነ ልቦና ዝግጅት የሚፈጥርላችሁ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ተቋቁሞ ውጤታማ መኾን የሚያስችላችሁን ስንቅ እንደያዛችሁ እንተማመንለን ነው ያሉት።
ዩኒቨርሲቲው አዳዲስ ሀሳቦችን የሚያመነጩ፤ ሥራ ፈጣሪ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ምሩቃንን ለማፍራት በተለያዩ መስኮች መፍትሔ ላይ ያተኮረ ጥናት እና ምርምር እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በተለይም በግብርና፣ በማዕድን፣ በቴክኖሎጂ፣ በባሕል እና ቱሪዝም ላይ ሀገራዊ እና ዓለማቀፋዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የልማት ፕሮጀክቶችን ለማሻሻል እየሠራ መኾኑን አንስተዋል።
የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ በሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች እና ማኅበረሰብ አቀፍ ድርጅቶች ጋር የሚኖረውን ትብብር ለማጎልበት የሚያስችል የ10 ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ ቀርጾ በመተግበር ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ትኩረት የተሰጣቸውን የሪፎርም ተግባራትን በትኩረት ይዞ እየሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሠብሣቢ ፕሮፌሰር ከፍያለው ዓለማየሁ ኢትዮጵያ ትምህርትን ለሁሉም የማዳረስ ሥራ እየሠራች መኾኑን ገልጸዋል። እኛም ለሀገር የምንከፍለው ዋጋ እጥፍ ድርብ መኾን አለበት ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የሚታይ ውጤት በማስመዝገብ የተግባር ሰው ኾነን መገኘት አለብን ነው ያሉት።
የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል እና የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ተማሪዎች ያገኛችሁትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ማኅበረሰቡን ማገልገል አለባችሁ ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
