የሌማት ቱርፋት መርሐ ግብር ዜጎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት እያሸጋገረ ነው።

4

 

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተቀረጸው የሌማት ቱርፋት መርሐ ግብር ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ይገኛል። ለመርሐ ግብሩ መሳካት የጎላ ድርሻ ያለው የንብ ማነብ ደግሞ በትንሽ መሬት እና በዝቅተኛ ገንዘብ በመጀመር ውጤታማ የሚያደርግ ዘርፍ ነው።

አስማሩ መኳንንት እና ጓደኞቻቸው የኅብረት ሽርክና ማኅበር በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ዞብል ክፍለ ከተማ በንብ ማነብ የተሠማሩ ናቸው። ማኅበሩ 210 አባላት አሉት። የማኅበሩ አባላት እንደገለጹት በሴፍትኔት ታቅፈው በቆጠቡት 400 ሺህ ብር መነሻነት ነው በ2017 ዓ.ም ወደ ንብ ማነብ ሥራ የገቡት።

የከተማ አሥተዳደሩ ባመቻቸላቸው 64 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ 50 የንብ ቀፎዎችን በማስቀመጥ እያለሙ ይገኛሉ። በሴፍትኔት እየተደረገላቸው የሚገኘውን ድጋፍ ተጠቅመው ነገን አልመው ራሳቸውን ከተረጅነት ወደ ሥራ ፈጣሪነት እያሸጋገሩበት መኾኑን ለአሚኮ ተናግረዋል።

የማኅበሩ አባል ወይዘሮ እናንዬ አቸነፍ ሁሌም ተረጅ ከመኾን ይልቅ ሥራ ፈጣሪ መኾን መቻላቸውን ገልጸዋል። የተሰጣቸውን መሬት አትክልት እና ፍራፍሬ በማልማት ለንቦች ምቹ ቀለብ ከመፍጠር ባለፈ የተራቆተ አካባቢን መልሰው እያለሙ መኾናቸውን አንስተዋል።

ሌላኛዋ የማኅበሩ አባል መቅደስ ንጉሤ እንደተናገሩት በእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ተቋም በኩል በቂ ሥልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ ገብተዋል። የሽግግር እና ዘመናዊ ቀፎዎችን በስፋት በመጠቀም ውጤታማ ለመኾን እየሠሩ መኾናቸውን ጠቁመዋል።

ሌላኛው በፋሲል ክፍለ ከተማ ያገኘናቸው አቶ ሞላ እሸቴ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ድርጅቶች ተቀጥረው መሥራታቸውን ነግረውናል። በጡረታ ዘመናቸው የሰው እጅ ጠባቂ ከመኾን ይልቅ መሥራትን በመምረጥ በንብ እርባታ ሥራ ተሠማርተው ይገኛሉ። በሦስት ቀፎዎች የጀመሩት ሥራ በአሁኑ ወቅት ከ40 በላይ ዘመናዊ ቀፎዎች በማድረስ ተጠቃሚ መኾናቸውን ነው የገለጹት።

በጎንደር ከተማ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት መምሪያ የንብ ሃብት ልማት ባለሙያዋ ዓለምነሽ ዘውዱ በዘርፉ ተሠማርተው ለሚገኙ አርቢዎች ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በሽግግር ቀፎ እና በዘመናዊ አሠራር ዙሪያ ሥልጠናዎች መሠጠታቸውም አንስተዋል። በዚህም ውጤት እያመጡ መኾኑን ነው የተናገሩት።

የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ መረጃ እንደሚያመለክተው በክልሉ ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ 32 ሺህ 642 ቶን የማር ምርት ተገኝቷል።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleነዳጅን በጥቁር ገበያ ለማዘዋወር መሞከር ጥብቅ እርምጃ ያስወስዳል።
Next articleዓለም እናንተን የሚቀበለው በያዛችሁት ዲግሪ ብቻ ሳይኾን በምትፈጥሩት ለውጥ ጭምር ነው።