“የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚዋጋው ሀገርን ለባዕድ አሳልፎ ለመስጠት ከሚባዝኑ ጠላቶች ጋር ነው” ለኦፕሬሽናል ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ

11

 

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ በጎጃም ተሰማርቶ ውጤታማ ግዳጅ እየተወጣ ለሚገኝ የጦር ክፍል አመራርና አባላት ስምሪት ሰጥተዋል።

ምክትል አዛዡ ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ እንደተናገሩት የዕዙ ሠራዊት በማንኛውም አካባቢ ሕዝብን ሠላም በሚነሱ ጽንፈኞች ላይ እርምጃ የመውሰድና ሕግን የማስከበር ተልዕኮውን በጀግንነት እየፈፀመ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚዋጋው ጀግኖች ቅድመ አያቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ውድ ሕይወታቸውን ገብረው ለዛሬ ትውልድ በክብር ያስረከቧትን ሀገራችንን ለባዕድ አሳልፎ ለመስጠት ከሚባዝኑ ጠላቶች ጋር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተላላኪው ጽንፈኛ የኢትዮጵያ ጠላቶችን ፍላጎት ለማሳካት ቢጥርም በአሁኑ ሰዓት ቀበሌ ይዞ መቆየት የማይችልበት ደረጃ የደረሰው በሀገር መከላከያ ሠራዊት በደረሰበት ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ መኾኑን ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ ተናግረዋል፡፡

ምሥራቅ ዕዝ ይህንን የሕዝብ ጠላት በገባበት እየገባ በመደምሰስ ላይ ይገኛል ነው ያሉት። በዚህ ሕግ የማስከበር ሂደት የአማራ ክልል ሕዝብ እና የፀጥታ ኃይል ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ ድርሻውን በመወጣቱ የዘራፊውን አላማ ለማክሸፍ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ዘገባው የምሥራቅ ዕዝ ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመረዳዳት በረመዳን እና በዒድ ብቻ የሚወሰን አይደለም።
Next articleነዳጅን በጥቁር ገበያ ለማዘዋወር መሞከር ጥብቅ እርምጃ ያስወስዳል።