
ደብረታቦር፡ መጋቢት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ)1ሺህ 447ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል በደብረ ታቦር ከተማ ተከብሯል።
ሙስሊም ማኅበረሰብ በረመዳን ወር ሲያከናውናቸው የነበሩ የመረዳዳት ተግባራትን አጠናክሮ በማስቀጠል ለሰላም ግንባታ የድርሻውን እንዲወጣም የከተማ አሥተዳደሩ አሳስቧል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን የረመዳን ወር የትዕግስት፣ የጸሎት እና የበጎ ተግባር መገለጫ መኾኑን ተናግረዋል። ማኅበረሰቡ እነዚህን እሴቶች ይዞ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ሼህ ማህመድ ጣሂር በዓሉ በድምቀት መከበሩን ገልጸዋል። እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ በረመዳን እና በዒድ ብቻ የሚወሰን ሳይኾን ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የበዓሉ ተሳታፊዎችም በዓሉ ከተለያዩ የሃይማኖቱ ተከታዮች ጋር ያለ ልዩነት በጋራ የሚከበር መኾኑን ገልጸዋል።
ወጣቶችን በመምከር እና በጋራ ጉዳዮች ላይ በመግባባት ሰላምን ለማምጣት የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል። ሰላምን ለማስፈን በጸሎት መትጋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ለሁሉም የምትበቃ ሀገርን ለመጠበቅ እና ለማስቀጠል በጸሎት መትጋት እና መምከር ተገቢ እንደኾነም ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
