
ደብረማርቆስ፡ መጋቢት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 1 ሺህ 447ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል በደብረ ማርቆሰ ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) ሁሉም ሃይማኖቶች በፀሎታቸው ለሀገር አንድነት በሰላም እና በአብሮነት ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ እስልምና ለሀገረ መንግሥት ምስረታ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከተ የሰላም እና የመቻቻል መሠረት ነው ብለዋል።
ሕዝበ ሙስሊሙ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል። የደብረ ማርቆስ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሠብሣቢ ሼህ ሙሀመድ ሽፋው ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የሃይማኖቱ አስተምህሮ የሚጠይቀውን በማድረግ በሰላም እና በአንድነት ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሸሪያ ፍርድ ቤት ዳኛ ሼህ ወለላው ሰኢድ በዓሉ ሕዝበ ሙስሊሙ ከፈጣሪ ምንዳ የሚያገኝበት ዕለት መኾኑንም ተናግረዋል። ዕለቱን በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሁነቶች በማክበር ለምስኪኖች አብሮነትን ማሳየት ይገባል ብለዋል።
ረመዳን ያለው ለሌለው የሚተሳሰብበት ታላቅ ወር መኾኑን ገልጸዋል። በበዓሉ ላይ ያገኘናቸው የሃይማኖቱ ተከታዮች ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በመከባበር እና በመተባበር ለሀገር ሰላም የበኩሉን አስተዋጽዖ ማበርከት አለበት ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
