
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሰጡትን የጥፋት ተልኮ ተሸክሞ ወደ ጋይንት የመጣው ጽንፈኛ ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት እና በክልሉ የጸጥታ አባላት እርምጃ ተወስዶበታል። በአካባቢው ሕግ በማስከበር ላይ የሚገኙት የሀገር መከላከያ ሠራዊት አመራር ኮሎኔል ዓለሜ ታደለ ጽንፈኛው ቡድን ለሕዝብ እና ለሀገር የማያስብ፣ ይልቁንም ኢትዮጵያን ጠል የኾኑ የላኪዎቹን አጀንዳ ተሸክሞ ክልሉን ለማተራመስ እየሞከረ ያለ ነው ብለዋል።
ከሰሞኑም ወደ ደቡብ ጎንደር ዞን ዘልቆ በመግባት የሕዝብ መገልገያ ንብረቶችን በመዝረፍ እና በማቃጠል የተለመደ ድርጊቱን ለመፈጸም ሙከራ አድርጓል ነው ያሉት። ይሁን እንጅ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በዚህ ቡድን ላይ አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ የአካባቢውን ሰላም እያስጠበቀ ነው ብለዋል። “ጋይንት ላይ የታቀደው የጽንፈኛው ቡድን እና የላኪዎቹ ህልም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ክንድ መክኗል” ነው ያሉት።
መከላከያ ሠራዊት ጥፋተኞችን ተከታትሎ በመያዝ ሕግ ያስከብራል፤ ከሀገር ጠላቶች ጋር ወግነው ሕዝብን ለማዋረድ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ ለአፍታም አይታገስም ነው ያሉት ኮሎኔሉ።
ጽንፈኛው ቡድን ጫካ ለጫካ ከመሹለክለክ ባለፈ በከተሞችም አካባቢ ጥቃቅን ትንኮሳዎችን በመጠነ ሰፊ የሀሰት ፕሮፖጋንዳው እያጀበ ሕዝብን ሰላም ለመንሳት እንደሚሞክርም ገልጸዋል።
አሁን ላይ ጋይንት እና አካባቢው ሰላም ነው፤
ሕዝቡም ለሀሰተኛ እና አደናጋሪ የጽንፈኞች ወሬ ጆሮውን በመንሳት በሙሉ ልቡ በልማቱ ላይ መሳተፍ አለበት ነው ያሉት። ከጸጥታ ኃይሎች ጎን በመቆም እና አካባቢውን ነቅቶ በመከታተልም ሰላሙን ለማወክ የሚጥሩትን አካላት መከላከል እንደሚገባው መልእክት አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
