መነሻቸውን ያረሱት በጎ አሳቢዎች።

8
ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “የተማርኩት ሳይማር ያስተማረኝን ሕዝቤን ለማገልገል ነው” የሚለው ብሂል በባሕር ዳር ከተማ ጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቀድሞ ተማሪዎች ኅብረት አማካኝነት ወደ ተጨባጭ ተግባር ተቀይሯል።
በ2010 ዓ.ም 12 ተማሪዎችን በመደገፍ የተጀመረው እና የጣና ቤተሰብ ስኮላርሺፕ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ በጎ ተግባር ዛሬ ላይ ተጠቃሚዎቹን ወደ 36 በማድረስ ስምንት ዓመታትን ማስቆጠሩን የትምህርት ቤቱ ምክትል ርእሰ መምህር ፀጋዬ ተፈራ ነግረውናል፡፡
ዋና ዓላማውም በትምህርት አቀባበላቸው ውጤታማ ኾነው ነገር ግን በኢኮኖሚ አቅም ማነስ ምክንያት ትምህርታቸውን ለመቀጠል ለሚቸገሩ ተማሪዎች የጀርባ አጥንት መኾን ነው።
ተማሪዎች የዕድሉ ተጠቃሚ ለመኾን ይችሉ ዘንድ ጥብቅ የምርጫ ሂደትን ያልፋሉ ብለዋል። የኢኮኖሚ ችግራቸው ከመረጋገጡ ባለፈ ከፍተኛ የውጤት መስፈርትን እንዲያሟሉ፤ የጽሑፍ ፈተና እንዲያልፉ እና ቃለ መጠይቅ እንዲያደርጉ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
የኅብረቱ ድጋፍ ከገንዘብ እርዳታ ባለፈ የተማሪዎችን ሁለንተናዊ ፍላጎት ያማከለ መኾኑ ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት። ቀደም ሲል በወር ከ200 እስከ 600 ብር ይደረግ የነበረው የገንዘብ ድጋፍ በአሁኑ ወቅት ወደ 1 ሺህ ብር ከፍ ማለቱንም ተናግረዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ለሴት ተማሪዎች የሚቀርበው የንጽሕና መጠበቂያ አቅርቦት በዓመት ለ500 ተማሪዎች የነበረው ወደ 1ሺህ ተማሪዎች ማሳደግ እንደተቻለ ገልጸዋል።
ማየት ለተሳናቸው ተማሪዎች የመቅረጸ ድምፅ መሣሪያዎችን ማቅረብ፣ የላቀ ውጤት ለሚያመጡ ተማሪዎች የልህቀት ሽልማት መስጠት እና ወደ ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡ ተማሪዎች ደግሞ የትራንስፖርት እና የጤና ዋስትና ድጋፎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ የኾነው የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነሲቡ በላይነህ ተማሪዎች አንድጊዜ ዕድሉን ካገኙ በኋላም በየዓመቱ ውጤታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ ስለሚያስገድዳቸው ከፍተኛ የኀላፊነት ስሜት እና ተወዳዳሪነትን ይፈጥርላቸዋል ብሏል።
ይህንኑ ተነሳሽነት መነሻ በማድረግ ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ የነበረውን የ96 በመቶ አማካይ ውጤት እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ማስቀጠል እንደቻለም ገልጿል፡፡ “እኔም ነገ እንደነ እርሱ መኾን እፈልጋለሁ” ሲልም ራዕዩን ነግሮናል።
የጣና ሐይቅ የቀድሞ ተማሪዎች (Alumni) ኔትወርክ የባሕር ዳር ከተማ አሥተባባሪ ተናኘ ፍቅሬ የጣና ሐይቅ የቀድሞ ተማሪዎች ኅብረት በዋናነት በኢኮኖሚ እጥረት ምክንያት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ የሚገደዱ ተማሪዎችን መታደግ እና የተማሩበትን ተቋም ማገዝን ዓላማው እንዳደረገ ገልጸዋል፡፡
ማኅበሩ ብቃት እያላቸው የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች ወርሃዊ የኪስ ገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ነው። በዚህ ዓመት ብቻ ከ10ኛ ክፍል እስከ መጀመሪያ ዓመት ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ 36 ተማሪዎችን እያገዘ ይገኛል ብለዋል፡፡
ከተማሪዎች የቀጥታ እርዳታ ባለፈ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚታዩ የመሠረተ ልማት ክፍተቶችን በመሙላት ላይ ማተኮሩንም ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት የመጸዳጃ ቤት አገልግሎቶችን ማሻሻል፣ የውኃ ፕሮጀክቶችን መዘርጋት፣ የቤተ ሙከራ ክፍሎችን ማደራጀት እና ሌሎች ሰፊ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።
በቀጣይም የድጋፍ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ለማሳደግ እና የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
አሥተባባሪው “ትውልድ የሚገነባው ከትምህርት ቤት ነው” በሚል የቀድሞ ተማሪዎች ለተማሩበት ተቋም ውለታቸውን እንዲከፍሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበቴክኖሎጂ ላይ እየተሰጡ ያሉ ሥልጠናዎች የወጣቶችን ሕይወት እየቀየሩ ነው።
Next article“ጋይንት ላይ የታቀደው የጽንፈኛው ቡድን እና የላኪዎቹ ህልም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ክንድ መክኗል” ኮሎኔል ዓለሜ ታደለ