ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በርካታ ጉዳቶችን አድርሷል። ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉት የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር በዞኑ ያለው የጸጥታ ችግር ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ማድረሱን ተናግረዋል።
በሰላም እጦት ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዲርቁ፤ የሕዝብ መገልገያ ተቋማት እንዲወድሙ፤ የእናቶች መገልገያ አንቡላንሶች እንዲቃጠሉ እና እንዲዘረፉ ኾነዋል ነው ያሉት።
የጸጥታ ችግሩ መንገድ እና መሰል መሠረተ ልማቶች በታቀደላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ እንቅፋት መፍጠሩንም ገልጸዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች የመንግሥትን የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ተሠርቷል ነው ያሉት።
አሁን ላይ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ያነሱት አሥተዳዳሪው ሕግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ ለሰላም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ውይይቶች እየተካሄዱ መኾናቸውንም ገልጸዋል። በሁለት ዓመት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን መቀበላቸውንም ተናግረዋል።
በተገኘው አንጻራዊ ሰላም የዞኑን ሕዝብ የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። በ2018 በጀት ዓመት 502 ልዩ ልዩ የልማት ፕሮጀክቶች በ20 ቢሊዮን ብር በጀት እየተሠሩ ይገኛሉ ነው ያሉት።
የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በመፍታት፤ ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ፤ የሌማት ትሩፋት ልማትን በማሳደግ፤ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ በማስቻል፤ የጤና አገልግሎትን በተገቢው መንገድ በማዳረስ እና በተለያዩ ዘርፎች ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡ የሰላም ባለቤት እንዲኾንም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
