የዶክተር አምባቸው መኮንን ፋውንዴሽን ጾታ ተኮር ጥቃትን ለመከላከል እና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል አዲስ ፕሮጀክት አስጀመረ።

4

ደብረብርሃን፡ መጋቢት፡09/2018ዓ.ም (አሚኮ) የዶክተር አምባቸው መኮንን ፋውንዴሽን በደብረ ብርሃን ከተማ ጾታ ተኮር ጥቃትን ለመከላከል እና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል አዲስ ፕሮጀክት አስጀምሯል።

ይህ ፕሮጀክት በተለይ በከተማዋ “ቻይና ካምፕ” ተብሎ በሚጠራው ጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ትኩረት የሰጠ ነው።

የዶክተር አምባቸው መኮንን ፋውንዴሽን መሥራች እና ዋና ዳይሬክተር መአዛ አምባቸው እንደገለጹት ተቋሙ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በጋይንት እና በፎገራ ወረዳዎች መሰል ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።

አሁን ላይ ደግሞ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖችን ለመደገፍ እና ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችል ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱ ማናጀር ዳንኤል አስፋው ፕሮጀክቱ ትኩረቱን በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ ለስድስት ወራት የሚቆይ ሲኾን በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ በለጥሽ ግርማ በከተማዋ ለችግር ተጋላጭ የኾኑ በርካታ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ በዘርፉ የሚሠሩ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ቁጥር አነስተኛ መኾኑን ገልጸዋል።

የዶክተር አምባቸው መኮንን ፋውንዴሽን የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ወደ ከተማዋ በመምጣቱ ምሥጋና አቅርበዋል።

በከተማዋ ያሉ ሌሎች መሰል ችግሮችን ለመቅረፍም ሌሎች ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በመጠለያ ጣቢያው የሚገኙ ሴት ተፈናቃዮች የአሁኑ አኗኗራቸው ለጾታዊ ጥቃት አጋላጭ መኾኑን ጠቁመዋል።

ፋውንዴሽኑ ይህንን ችግር ለመቅረፍ መምጣቱ ትልቅ እፎይታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ሥነ ጊዮርጊስ ከበደ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም ከፍተኛ የኾነ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና አቅም የሚጠይቅ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ