
ባሕርዳር፡መጋቢት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና ከተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ጋር በመተባበር የኮሌራ ወረርሽኝን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል የንቅንቄ መድረክ አካሂዷል።
በአማራ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የበሽታዎች እና ሌሎች ጤና አደጋዎች ቅኝት እና ምላሽ አሰጣጥ ባለሙያ ወንደሰን የኋላ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኮሌራ ወረርሽኝን ለመከላከል እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
በሃይማኖት ተቋማት አካባቢ ያለውን የግል እና የአካባቢ ንጽሕና አጠባበቅን ለማሻሻል ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል። በአማራ ክልል ስድስት ሰው የሚበዛባቸው የሃይማኖት ሥፍራዎች ተለይተው ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር፤ የግል እና የአካባቢ ንጽሕናን ለመጠበቅ የሚረዱ መጸዳጃ ቤቶች፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃ እና መሰል ተቋማት እየተገነቡ መኾናቸውን አንስተዋል።
የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ቦርድ ተወካይ መላከ ብርሃን ፍሰሀ ጥላሁን ኮሌራ በጥንቃቄ ጉድለት እንደሚከሰት ተናግረዋል። የሚመለከታቸው ተቋማት ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመተባበር በሚያከናውኑት የመከላከል ሥራ በሽታው የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ተደርጎል ነው ያሉት።
የሃይማኖት አባቶች ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ወረርሽኙን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የፕሮግራሞች ዳይሬክተር ደሳለኝ ለጅቦ ኮሌራ በንጽሕና ጉድለት የሚከሰት እና በአጭር ጊዜ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ገዳይ በሽታ በመኾኑ በአምልኮ ቦታዎች እንዳይከሰት ትኩረት ያስፈልገዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ጉባኤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በሽታውን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የሃይማኖት ተቋማትን ሙሉ በሙሉ ከወረርሽኙ ነጻ ለማድረግ በንቅናቄ እየተሠራ ነው ብለዋል። ንቅናቄው
በሽታውን ከኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ የማስወገድ ዓላማ እንዳለውም ተናግረዋል።
የሃይማኖት አባቶች በአምልኮ ሥፍራዎች መጸዳጃ ቤት፣ ሻወር እና መታጠቢያ ቦታዎችን በማዘጋጀት ኮሌራን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ በትኩረት እንዲሠሩም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ አማካሪ ወልደ ትንሳኤ መኮንን (ዶ.ር) ኮሌራ አስከፊ በሽታ ነው ብለዋል። የኮሌራ ወረርሽኝ ሲከሰት የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መኾኑንም ገልጸዋል። በሽታውን ቀድሞ መከላከል በብዙ መልኩ አትራፊ ያደርጋል ነው ያሉት።
በአምልኮ ሥፍራዎች እና ሰው በሚበዛባቸው አካባቢዎች በሽታው እንዳይከሰት ቀድሞ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶችም በሽታው እንዳይከሰት እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ ጤና ቢሮ ድጋፍ በሃይማኖት ተቋማት መጸዳጃ ቤት እና የንጹሕ መጠጥ ውኃ እየተገነባ መኾኑንም ተናግረዋል። የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራውንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
