
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር “ለሰላም ዘብ እንቆማለን የልማት አርበኛ እንኾናለን” በሚል መሪ መልዕክት ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርጓል።
የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ.ር) የክልሉ ቀዳሚ አጀንዳ ሰላም ነው ብለዋል። ውጫዊ እና ውስጣዊ ኀይሎች ተቀናጅተው የክልሉ ሰላም እንዳይረጋጋ እየሠሩ መኾኑን አንስተዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት መንግሥት ሁሉንም የሰላም አማራጮች ተጠቅሟል፤ አሁንም ለሰላማዊ አማራጭ በሩ ክፍት ነው ብለዋል። መምህራን የጠላትን አጀንዳ በመገንዘብ የጋራ አቋም መያዝ እና ለሰላም መቆም እንደሚገባቸውም አንስተዋል።
መምህራን የችግሩን አሳሳቢነት በአግባቡ ተረድተው የጥፋት ኀይሎችን በጋራ መመከት እንደሚገባቸው ተናግረዋል። የተጀመሩት የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም አሳስበዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በሰላማዊ አስተሳሰብ የተቃኘ እና በአመክንዮ ላይ የተመሠረተ ትውልድ ለመፍጠር የመምህራን ሚና የላቀ ነው ብለዋል።
በከተማዋ የተሠሩት ልማቶች የመጡት በመደማመጥ እና በመደጋገፍ መኾኑን ገልጸዋል። መምህራንም ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ እና የመደማመጥ ባሕል እንዲዳብር ከመንግሥት ጎን ኾነው በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባም አንስተዋል።
የመምህራን ልማቱ ትውልድን መቅረጽ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የነቃ ትውልድን በመፍጠር የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት እንዲወጡም አሳስበዋል። በሰላም ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ስንታየሁ ነጋሽ መምህራን ትውልድን የመቅረጽ ትልቅ ኀላፊነት አለባቸው ብለዋል።
የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመጋፈጥ ትውልድን ከውድቀት መታደግ እንደሚገባቸውም አንስተዋል።
ዘጋቢ:-አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
