
ባሕር ዳር: መጋቢት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ “የብሔራዊ ንግድ እና ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርኃ- ግብር ሰነድ” ዝግጅት ግብዓት ማሰባሰቢያ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ መካሄድ ተጀምሯል፡፡
የኢፌድሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሰብዓዊ መብት ዳይሬክቶሬት ጀነራል አወል ሱልጣን ለተሳታፊዎች የመድረኩን ዓላማ አብራርተዋል። ኢትዮጵያ የመርኃ-ግብር ሰነዱን ማዘጋጀቷ ልማትን በማሳለጥ ዜጎች እና የንግዱ ማኅበረሰብ በድርጊት መርኃ ግብሩ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ ያመቻቻል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩልም በተባበሩት መንግሥታት በተሰጠው ምክረ ሀሳብ መሠረት በዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ በዘርፉ እውቅና ለማግኘት፣ ሰብዓዊ መብትን እና ልማትን ለማሳለጥ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
የዩኤንዲፒ የገቨርናንስ ቲም ኃላፊ ፍስሃ መኮንን ድርጅታቸው የንግድ እና የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርኃ ግብር በኢትዮጵያ እንዲኖር በማድረግ የንግድ እና ሰብዓዊ መብት እንዲሳለጥ በተለያየ መንገድ እየደገፉ መሆኑን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አያሌው አባተ (ዶ.ር) የሲቪል ማኅበረሰብ ንግድ በሕግ ውስጥ ቦታ የተሰጠው መኾኑን አስረድተዋል።
ከሰብዓዊ መብት ጋር ያለውን ቁርኝት ታሳቢ ባደረገ መንገድም በዘርፉ ያሉ የሕግጋትን እና የአሠራር ክፍተት የሚሞላ በመሆኑ ይህንን መሰል የድርጊት መርኃ-ግብር ማዘጋጀት ማስፈለጉን ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎችና ተወካዮች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህራን፣ ዐቃቤ ሕጎች፣ ዳኞች እና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡
የውይይት መድረኩ የተዘጋጀው በኢፌድሪ ፍትሕ ሚኒስቴር፣ በዩኤንዲፒ እና በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ትብብር ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
