ተቋማት የልማት እና የሰላም አንባሳደር መኾን አለባቸው።

3

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት “ለሰላም ዘብ እንቆማለን፤ የልማት አርበኛ እንኾናለን” በሚል መሪ መልዕክት በከተማዋ ካሉት የፌዴራል ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።

የጉምሩክ ኮሚሽን ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ አለነ መሃሪ ተቋሙ ፈተናዎችን በመቋቋም በተለያዩ አካባቢዎች የሕገ ወጥ ተግባራት ቁጥጥር ሥራዎችን እያከናወኑ እንደኾነ ተናግረዋል።

የሀገር ውስጥ እና የውጭ ንግድ ሥራዎች ይሠራሉ፤ ነገር ግን በጸጥታ ችግሩ ምክንያት የመንገዶች መዘጋት እና የአሽከርካሪዎች እገታ ፈተና እንደኾነ አንስተዋል። ይህ ደግሞ የሰላም እጦት የወለደው ዳፋ ነው ብለዋል።

የሰላም እጦት የሚያስከትለውን የኢኮኖሚ ድቀት እና የልማት መስተጓጎል ለማኅበረሰቡ በማስረዳት የሰላም በር ለመኾን እንደሚሠሩም ገልጸዋል።

የመደማመጥ እና የመነጋገር ባሕል አለመኖር ለበርካታ ችግሮች ዳርጎናል ያሉት ደግሞ በባሕር ዳር ፀደይ ባንክ ጊዮን ቅርንጫፍ ሥራ አሥኪያጅ ሁነኝ ዘገዬ ናቸው። የሀገርን ህልውና ለማስቀጠል ከልብ መወያየት ያስፈልጋል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም መንግሥት ሰላም እና መረጋጋት እንዲረጋገጥ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ሰላምን የሚያውኩ የውጭ እና የውስጥ ጠላቶችን ለመከላከል አንድነትን ማጠናከር ወሳኝ ነውም ብለዋል።

ሰላምን በማጽናት እና ልማትን በማረጋገጥ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግም ነው የገለጹት።

ተቋማት ቀልጣፋ እና ፈጣን አገልግሎት መስጠት እንደሚጠበቅባቸውም ኀላፊው አንስተዋል። “ተቋማት የልማት እና የሰላም አንባሳደር መኾን አለባቸው” ነው ያሉት።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ደ.ር) የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር እና ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት ሕገ ወጥነትን እና ሌብነትን መከላከል ይገባል ብለዋል። ለዚህም ሁሉም ከልብ በመነጨ አኳዃን መሳተፍ አለበት ነው ያሉት።

ሁሉም የሰላም እና የልማት አርበኛ መኾን እንዳለበትም በመድረኩ ተነስቷል።

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዓድዋ ድልን እና የእቴጌ ጣይቱን ግለ ታሪክን የሚያትት መጽሐፍ ተመረቀ።
Next article“ፊቼ ጫምባላላን ስናከብር አንድነት እና ኅብረታችንን በማጠናከር ሊኾን ይገባል” የሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ