ሰላምን ለማጽናት አጥፊዎችን መታገል ይገባል።

9
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከደሃና ወረዳ እና ከአምደ ወርቅ ከተማ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የሰላም እጦቱ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመትን እያደረሰ እንደሚገኝ አንስተዋል። ከልማት በፊት ሰላም ይቀድማል ያሉት ነዋሪዎቹ ሰላምን ለማጽናት ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።
መንግሥት የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን በቁርጠኝነት ሰላምን ማስፈን እንዳለበትም አንስተዋል። ደረጃውን የጠበቀ የመንገድ መሠረተ ልማት እንዲሠራላቸውም ጠይቀዋል።
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ ሹመት ጥላሁን ነዋሪዎቹ የጸጥታ አካላትን በመደገፍ እና መረጃ በመስጠት ለሰላም እንዲሠሩ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ወደ ገበያ እንዲያቀርቡ፣ የተጀመሩ መሠረተ ልማቶች እንዲጠናቀቁ፣ የንግድ ሥርዓቱ የተቀላጠፈ እንዲኾን እና የኑሮ ውድነት እንዲቀንስ ሰላምን ማስጠበቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የሃይማኖት አባቶች ሃይማኖታዊ ሥርዓትን በማስተማር እና ታጣቂዎችን የሰላም መንገድ በማመላከት የአባትነት ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) ማኅበረሰቡ ልጆቹን በመምከር የሰላምን አማራጭ እንዲቀበሉ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።
በግጭት የሚፈታ ችግር ባለመኖሩ በውይይት ችግሮች እንዲፈቱ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ታጣቂዎች እንዲቀበሉ ማኅበረሰቡ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበትም ተናግረዋል።
የምርጫ ካርድ በማውጣት እና በምርጫ ሂደቱ በመሳተፍ ስኬታማ ምርጫ እንዲከናወን ማኅበረሰቡ የበኩሉን እንዲወጣም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ተማሪዎች ተመራማሪ የሚኾኑት፣ የሀገርን ኢኮኖሚ የሚገነቡት እና ያስተማራቸውን ማኅበረሰብ ማገልገል የሚችሉት ሰላም ሲኖር በመኾኑ ሰላምን ማጽናት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የሕዝብን አብሮነት ለማጥፋት የሚሠሩ ታጣቂ ኀይሎች በመኖራቸው ሰላምን ለማጽናት ጥፋትን መታገል ይገባል ብለዋል።
ምርጫ ፓርቲን ወደ ሥልጣን ለማምጣት እና ከሥልጣን ለማውረድ የሚደረግ ሂደት ብቻ ሳይኾን የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ፣ የአሥተዳደር አንድነትን ለማጽናት እና የሕዝቦችን ወንድማማችነት ለማስጠበቅ የሚካሄድ ነው ብለዋል።
ሕዝብን በልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የአዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ፣ የዶሮ ጫጩት መፈልፈያ ፋብሪካ እና ሌሎች ልማቶች እየተሠሩ መኾኑንም አንስተዋል።
የተጀመሩ እና የተቋረጡ የመንገድ መሠረተ ልማቶች እንዲጠናቀቁ ወደ ሥራ መገባቱንም አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበያዝነው ወር በአንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ የሙቀት መጠን ይኖራል።
Next articleበኢትዮጵያ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሀዘን ታወጀ።