የፍላጎት ማሳኪያ መንገዶች ሰላማዊ አማራጮች ብቻ መኾን አለባቸው።

6

 

እንጅባራ፡ መጋቢት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር “ለሰላም ዘብ እንቆማለን፣ የልማት አርበኛ እንኾናለን” በሚል መሪ መልዕክት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከወጣቶች ጋር ተወያይቷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በክልሉ ሕዝብ ላይ በርካታ ሰብዓዊ እና ማኅበራዊ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል። የተቋማት ውድመት ማስከተሉንም ተናግረዋል።

የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እንዳይባባስ በማድረግ ለአካባቢያቸው ሰላም መሻሻል ገንቢ ሚና መጫወታቸውንም ገልጸዋል።

የውስጥ እና የውጭ ጠላቶችን የተቀናጀ ሴራ ለማምከን ዝግጁ መኾናቸውን ያነሱት ወጣቶቹ “በእኛ ጊዜ የሚገነባ እንጂ የሚፈርስ ሀገር አይኖረንም”
ብለዋል።

የፍላጎቶቻችን ማሳኪያ መንገዶች ሰላማዊ አማራጮች ብቻ መኾን እንደሚገባቸውም ነው የተናገሩት።

ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እና የማኅበረሰቡን የኑሮ ጫና የሚያቃልሉ ሥራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ጠይቀዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ባለፉት ዓመታት በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ እንዳይባባስ በማድረግ ወጣቶች ገንቢ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።

የሰላም አማራጮችን በማቅረብ እና ማኅበረሰቡን ለልማት በማስተባበር ለዘላቂ ሰላም ግንባታ መትጋት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

የውስጥ ባንዳዎች እና የውጭ ባዳዎች ተቀናጅተው የሀገራችንን ሰላም ለማወክ እየሠሩ ነው ያሉት አሥተዳዳሪው ወጣቶች ወቅታዊ ሁኔታን ያገናዘብ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

መንግሥት የወጣቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማሳደግ አቅዶ እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል። ዕቅዶቹ ተፈፃሚነት የሚኖራቸው ግን የጸና ሰላም ሲኖር ነው ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለጥንቃቄ
Next articleየአማራ ባንክ በጠንካራ እና የተረጋጋ የፋይናንስ አቋም ላይ ኾኖ እየሠራ መኾኑን አስታወቀ።