በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በንቃት መካከል ይገባል።

7

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ አስተናጋጅነት በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለመከላከል እና የተቋማትን ቅንጅት ለማጠናከር ያለመ የባለድርሻ አካላት የውይይት እና የሥልጠና መድረክ እየተካሄደ ነው።

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኀላፊ አያሌው አባተ (ዶ.ር) ክልሉ ካለበት ወቅታዊ የግጭት ሁኔታ አንጻር በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚሠሩ ተግባራት በከፍተኛ ትኩረት ሊከናወኑ ይገባል ብለዋል።

በክልሉ የ25 ዓመታት አሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት
ዕቅድ ውስጥ የሴቶች፣ ሕጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ አንዱ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መኾኑንም ተናግረዋል። የፍትሕ ቢሮውም ይህንን ጉዳይ እንደ አንድ ትልቅ ግብ ይዞ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከዕቅዱ ባሻገር ተቋማዊ አደረጃጀት ለሥራው ስኬታማነት ወሳኝ መኾኑን እና በሂደትም የሰው ኃይል የማሟላት ሥራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

ለሥራው ውጤታማነት ፈጻሚ አካላትን በሥልጠና ማብቃት አስፈላጊ መኾኑን የገለጹት ምክትል ኀላፊው
ለዚህም ይረዳ ዘንድ ሥልጠና እየተሰጠ መኾኑን አስታውቀዋል።

በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ድንበር የማይመርጡ በመኾናቸው መሰል ወንጀሎችን ለመከላከል ሁልጊዜም ዝግጁ መኾን እና በንቃት መጠበቅ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ወንዳቸው ሠራው አካላዊ፣ ጾታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶች የሚያደርሱትን ዘርፈ ብዙ ጉዳት ለመቀነስ የተቋማት ቅንጅት ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል።

እነዚህን ጥቃቶች ለመከላከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ ትግል እና ውይይት ሲደረግ መቆየቱን ያስታወሱት ምክትል ኀላፊው በኢትዮጵያም ጥቃቶችን ለመግታት የተለያዩ ሕጎች መውጣታቸውን፣ የፌዴራል እና የክልል ተቋማትም በተሰጣቸው ሥልጣን እና ኀላፊነት ሕጎቹን በማስፈጸም ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በአማራ ክልልም ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የደረሱ 200 የጥቃት ጉዳዮች ተመዝግበዋል ብለዋል። ለእነዚህም አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በተደረገው ጥረት አብዛኛዎቹ ውሳኔ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ወንጀለኞችን ለሕግ አቅርቦ የማስቀጣት አቅም 94 በመቶ መድረሱን ነው የተናገሩት። ይህም የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየተከናወነ ያለውን ጠንካራ ሥራ የሚያሳይ መኾኑን ጠቁመዋል።

በፍትሐብሔር የፍትሕ አሥተዳደር ዘርፍ 700 የሚጠጉ መዝገቦች ታይተዋል። ከ422 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ጉዳዮች እልባት ማግኘታቸውም ተገልጿል።

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሀገር የሚገነባው በሕሊናዊ መንፈስ ነው” ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
Next articleበዱር እንስሳት እና በኢኮ ቱሪዝም ዘርፍ የታየው ዕድገት ዓለም አቀፍ ጎብኝዎችን እየሳበ ነው።