የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ሁሉም ድጋፍ ማድረግ አለበት።

4
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ​በአማራ ክልል በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት ከ6ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ተጎድተዋል። በዚህም በርካታ ታዳጊ ተማሪዎች በዕድሜ ደረጃቸው መቅሰም ሚጠበቅባቸውን ዕውቀት እንዳይገበዩ አድርጓል። ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከልም የሰሜን ወሎ ዞን ተጠቃሽ ነው።
በዞኑ 563 የትምህርት ተቋማት ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል። እነዚህም በተለያዩ ድጋፎች መልሶ የመገንባት ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ከትምህርት መምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረገችው በሀብሩ ወረዳ የአቢወት ፍሬ አንደኛ እና መካካለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነኢማ ሰይድ ትምህርት ቤታቸው በመውደሙ ለሥነ ልቦና ጉዳት ተዳርጋ እንደነበር ታስታውሳለች። ተስፋ በመቁረጥ ወደ ሌላ አካባቢ ለመሄድ እሳቤ እንደነበራትም ገልጻለች።
በኋላ ትምህርት መልሶ ቢጀመርም በሸራ በተሠራ ክፍል ነፋሱ፣ ብርዱ፣ የፀሐይ ሀሩሩ እና አቧራው እያረፈባቸው ሲማሩ ቆይተዋል።
ዛሬ ላይ ግን ትምህርት ቤቱ በአዲስ ተገንብቶ በተመቻቸ ክፍል ውስጥ በመማሯ ደስተኛ መኾኗን ተናግራለች።
ትምህርት ቤቱ ታደገኝ ያለችው ተማሪዋ ወላጆቿም ነገ የተሻለ ደረጃ በመድረስ እንደምታግዛቸው ተስፋ መሰነቃቸውን ትናገራለች ።
የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሰጠ ታደሰ በዞኑ 61ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች እና በፌዴራል መንግሥት መልሰው መገንባታቸውን ተናግረዋል። ሌሎችም በማኅበረሰቡ ተሣትፎ ጥገና እየተደርገላቸው መኾናቸውን ነው የገለጹት።
በተለይ ተማሪዎች ደረጃቸውን በጠበቁ እና በምቹ ትምህርት ቤቶች በመማራቸው የመቅረት ምጣኔን መቀነስ እና ውጤታቸውን ማሻሻል ተችሏል ነው ያሉት። ለትምህርት ጥራትም ከፍተኛ ድርሻ አለው የሚሉት ኀላፊው አሁንም ድጋፍ የሚፈልጉ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን አንስተዋል።
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሲቪል ምህንድስና ዳይሬክተር ሚካኤል ንብረት በአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ጋር በቅንጅት ባለፈው ዓመት ብቻ 22 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን ተናግረዋል። በጥራት እንዲገነቡ ክትትል መደረጉንም አንስተዋል። ትምህርት ቤቶችን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መኾኑን አስገንዝበዋል።
በዚህ ዓመትም 63 የትምህርት ተቋማት እየተገነቡ መኾናቸውን ተናግረዋል። ይህም በተማሪዎች ዕውቀት እና የትምህርት አቀባባል ምቹ ሁኔን እየፈጠረ ነው ብለዋል። ብቁ እና ተወዳዳሪ ተማሪዎች ለማፍራት የትምህርት ተቋማቱ መገንባት ትልቅ ድርሻ እንዳለው አንስተዋል።
በአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አባተ ጌታሁን (ዶ.ር) ጽሕፈት ቤቱ በክልሉ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት መልሶ ለማልማት እና ለመገንባት 1ሺህ 370 ኘሮጀክቶችን ይዞ በ18 ዞኖች እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ከተለያዩ መንግሥታዊ ካልኾኑ ረጂ ድርጅቶች፣ ከተቋማት፣ ከፌዴራል እና ከሌሎችም አካላት ከ13ቢሊዮን ብር በላይ በማሠባሠብ የተቋማት መልሶ ግንባታ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። በትምህርት ዘርፍ ከ4 ነጥብ 1ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ 451 ትምህርት ቤቶችን በ10 ዞኖች የመልሶ ግንባታ ተግባራት ማከናወን ተችሏል ነው ያሉት። የግንባታ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
በአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለማልማት 300ሺህ መጽሐፍትን፣ 41ሺህ የኮምባይንድ ዴስክ፣ 35 ኮምፒውተር ድጋፍ ማድረጉንም ጠቁመዋል።
በዕውቀት፣ በክህሎት እና በአመለካት የበቃ መልካም ሥነ ምግባር ያለው ትውልድ መገንባት የሚቻለው ደረጃውን በጠበቀ እና በተመቻቼ ትምህርት ቤት ታዳጊዎችን መቅረጽ ሲቻል ነው ብለዋል። ከችግሮች ለመውጣት እና የትውልድ ስብራትን ለመጠገን ሁሉም ድጋፍ ማድረግ እና መሥራት እንደሚገባው አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ውጤታማ ምርጫ ለማካሄድና ሰላምን ለማጽናት በጋራ መሥራት ያስፈልጋል” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleየፎቶ እና የቪዲዮ ማቀነባበሪያ ሶፍትዌሮች መበራከትን ለሐሰተኛ መረጃ ስርጭት የመጠቀም አባዜ።