
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር መሪዎች ጋር በወቅታዊ የሰላም፣ የጸጥታ፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው መንግሥት ለመመስረት ውጤታማ እና ስኬታማ ምርጫ እንዲከናወን መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የአካባቢን ሰላም ሕዝብን ደጀን በማድረግ ማጽናት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። በሌማት ቱሩፋት፣ በግብርና ሥራዎች፣ በተለያዩ ዘርፎች የሥራ ዕድልን በመፍጠር ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ ልማትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በጠራ አመለካከት ስኬታማ ተግባርን ማከናወን እንደሚያስፈልግም አንስተዋል። የሥራ ኀላፊዎቹ በችግር ውስጥም ቢኾን የግብርና ሥራን በማስቀጠል፣ የገቢ አሠባሠብን በማጠናከር፣ የትምህርት ዘርፉን ውጤታማ በማድረግ እና በሌሎች ዘርፎችም ውጤታማ ተግባር እንዲያከናውኑ አሳስበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ የአካባቢውን አንጻራዊ ሰላም ለማስጠበቅ እየተሠሩ ያሉ ተግባራት የሚደነቁ መኾኑን አንስተው አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
የበለጸገች ሀገር ለመገንባት እንቅፋቶችን በማስወገድ ጠንካራ መሪ መፍጠር እንደሚገባም ጠቁመዋል። ማኅበረሰቡ የምርጫ ካርድ እንዲያወጣ በትኩረት መሠራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) የጥፋት ኀይሎች ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እንዳይካሄድ፤ ሕዝባዊ መንግሥት በምርጫ ሂደት እንዳይቋቋም እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።
የአካባቢን ሰላም በማጽናት የምርጫ ሂደቱ ስኬታማ እንዲኾን በትጋት መሥራት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
በቀጣይ አንድነትን በማጠናከር በጋራ መሥራትን ማስቀጠል እንደሚገባም ተናግረዋል።
በውይይቱ ማኅበረሰቡ የዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያን እንዲያወጣ መደረጉ፤ የገጠር ኮሪደር ልማት ለማስጀመር የቦታ ልየታ ሥራ መከናወኑ፤ ስደትን ለመቀነስ መሠራቱ፤ የአካባቢውን አንጻራዊ ሰላም ከማስጠበቅ አንጻር ጠንካራ ሥራ መከናወኑን የውይይቱ ተሳታፊ የሥራ ኀላፊዎች ተናግረዋል።
የታዩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል ክፍተቶችን በማስተካከል የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
