በኢትዮጵያ ጠንካራ የስደተኞች አሥተዳደር እና የድንበር ጤና ጥበቃን ለማገዝ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ኾነ።

8

 

አዲስ አበባ፡ መጋቢት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኔዘርላንድ ኤምባሲ ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ስልታዊ የስደተኞች አሥተዳደርን ለመዘርጋት የሚያስችል አዲስ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።

ፕሮጀክቱ በዋናነት ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ውሥብሥብ የስደተኞች ፍሰት በበላይነት ለመቆጣጠር እና የድንበር ላይ መሠረተ ልማቶችን ለማሳደግ ያለመ ነው።

ለዚህ ፕሮጀክት የ5 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተመድቧል። ዋና ዓላማውም በድንበር አካባቢ ያለውን የስደተኞች እንቅስቃሴ ጤናማነት ማረጋገጥ፣ የመንግሥትን የቁጥጥር ሥርዓት ማጠናከር፣ የድንበር መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት እና የመረጃ አሥተዳደርን ማዘመን ነው ተብሏል።

ይህም ኢትዮጵያ በድንበር አካባቢ ለምታደርገው የተቀናጀ ቁጥጥር ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ታምኖበታል።

በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ክርስቲኒ ፒረኒ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠር ኪሎ ሜትር የድንበር ክልል ያላት በመኾኑ እና የምሥራቅ፣ የደቡብ እና የሰሜን የስደተኞች መተላለፊያ ማዕከል በመኾኗ ጉዳዩን ውሥብሥብ እና ተለዋዋጭ ያደርገዋል።

በመኾኑም በድንበር አካባቢ የሚደረግ ስደት ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ጠንካራ አሥተዳደር እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ መኾኑንም ጠቁመዋል።

ኔዘርላንድ ቀደም ሲል ከኢትዮጵያ ጋር ሥትሠራ የነበረውን የዘርፉን ተግባር በዚህ ፕሮጀክት አጠናክራ እንደምትቀጥልም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ ኢትዮጵያ በስደተኞች ጤና ዙሪያ ከዓለም አቀፍ የጤና እና የስደተኞች ድርጅቶች ጋር በቅንጅት ሥትሠራ መቆየቷን አስታውሰዋል።

አዲሱ ፕሮጀክት በተለይም ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ተላላፊ በሽታዎችን ለመቆጣጠር ለያዘችው ሀገራዊ ዕቅድ ትልቅ አጋዥ እንደሚኾን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሳምባ ምች በሽታን በምን መከላከል ይቻላል ?
Next articleየምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መልእክት፦