
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭት በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት አድርሷል። የግጭት ወቅቶች ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በክልሉ የሚያዝኑ እናቶች የተበራከቱት፣ የሀገር እና የሕዝብ ንብረት የወደመበት እና መኾን የሌለባቸው ነገሮች ሁሉ የኾኑበት ነበር።
ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዲጅታል ሚዲያ ሀሳባቸውን የሰጡ የጣቁሳ ወረዳ ደልጊ ከተማ ነዋሪ እንደሚሉት መንግሥት በወሰዳቸው ርምጃዎች አንጻራዊ ሰላም ቢስተዋልም አሁንም ቢኾን ታጣቂ ቡድኑ ሰርጎ እየገባ በሚከፍታቸው ግጭቶች የሰው ሕይወት እየቀጠፈ እና የሕዝብ ንብረት እያወደመ ነው። በዚህም ሕዝቡ በከፍተኛ ሁኔታ ተማሯል ብሎናል።
“አካባቢው ባለፉት ጊዜያት ሰላማዊ ኾኖ የከረመ ቢኾንም ሰሞኑን ታጣቂ ቡድኑ ተሹለክልኮ በመግባት ደልጊ ከተማ ገብቶ ከተማዋን እንዳልነበረች አድርጓታል” ብለዋል። የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማትንም አውድሟል። የግለሰቦችን ንብረትም ዘርፏል ነው ያሉት።
የወረዳው ማኅበረሰብ ግጭት ፈጽሞ አይፈልግም ያሉት ነዋሪው ባለፉት ጊዜያት ሰላሙን አስጠብቆ የቆየውም ለዚሁ ነው ብለዋል።
ሌላው የቡሬ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪም ታጣቂ ቡድኑ በሚከፍተው ግጭት፣ በሚፈጽመው ዘረፋ፣ እገታ እና ግድያ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ መከራ አስተናግዷል ብለዋል።
ግጭቱ በተጀመረበት ሰሞን ባለማወቅ ከግጭት ጠማቂዎች ጎን የቆሙ ነዋሪዎች እንደነበሩ አስታውሰው ከረፈደም ቢኾን የታጣቂ ቡድኑን ግፍ ተገንዝበው እየተቃወሙት መኾኑን አስረድተዋል።
ታጣቂ ቡድኑ በሚገኝባቸው አንዳንድ ገጠራማ አካባቢዎች አርሶ አደሮችን እህል እና ገንዘብ አዋጡ እያለ እንደሚያስገድድ፤ ከመንግሥት ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል ነዋሪዎችን እንደሚገድል፤ በርካታ ሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት እንደሚፈጽም ገልጸዋል። መንግሥት ለእነዚህ ነዋሪዎች መድረስ ይገባዋልም ነው ያሉት።
ማኅበረሰቡ የግጭትን አስከፊነት እና የሰላምን አስፈላጊነት ጠንቅቆ ተገንዝቧል ያሉት ነዋሪዎቹ አሁን ላይ የማኅበረሰቡ ጸሎት ሰላም ብቻ ኾኗል ብለዋል። ሰላምን ለማስፈን ከመንግሥት ጎን ኾነው እየሠሩ እንደሚገኙም አረጋግጠዋል።
ክልሉን ሙሉ በሙሉ ወደ ሰላም ለመመለስ መንግሥት የታጣቂ ቡድኑን የሎጀስቲክ ምንጭ በማድረቅ፤ የዘረፋ፣ የግድያ እና የእገታ ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎችን ተከታትሎ በመያዝ አስተማሪ ቅጣት በመቅጣት፤ የታጣቂ ቡድኑ የመረጃ ምንጭ የኾኑ አካላት ላይ ርምጃ በመውሰድ፤ ማኅበረሰቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ፤ የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን ቆጥሮ በመፍታት ክልሉ ወደ ሰላም እንዲመጣ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለመደበኛ ግዳጁ ሲል ቦታዎችን ለቅቆ ወደ ሌላ ሲንቀሳቀስ ጽንፈኛ ቡድኑ ተሹለክልኮ በመግባት አንዳንድ ከተሞችን ለመረበሽ ሞክሯል ብለዋል። የክልሉ መንግሥት በራሱ አቅም ጸጥታውን ለማስከበር የጸጥታ ኀይሎችን እያደራጀ እና እያጠናከረ፤ የታጣቂዎችን ህልምም እያመከነ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም ሰርጎ ገብ የጽንፈኛ ቡድኖችን እየጠቆመ እያስያዘ ነው፤ ከአካባቢው በማስወጣትም ሰላሙን እየጠበቀ ነው ብለዋል ቢሮ ኀላፊው።
ማኅበረሰቡ ጽንፈኛ ቡድኑን ከማውገዝ ባለፈ ሽፍታ ሊኖር አይገባም ብሎ አቋም መያዝ እና በመምከር ጭምር ማስተካከል እንዳለበትም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
