“የባሕሩን ታሪክ የት ይደብቁታል፣ እንኳንስ ሰዎቹ ግመሎች ያውቁታል”

7
ባሕር ዳር: መጋቢት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ዙፋን ነው፤ ንግሥናን ያደመቀችበት፤ ኃያልነቷን ያሳየችበት። ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ድልድይ ነው፤ ከሌሎች ዓለማት ጋር የተገናኘችበት፤ የሚመጣውን የተቀበለችበት፤ የሚሄደውን የሸኘችበት።

ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ሰገነት ነው፤ ከአድማስ ባሸገር የምትመለከትበት፤ ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ገበያ ነው፤ ንግዷን ያቀጣጠለችበት፤ ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ቀለም ነው፤ ከጥንት ጀምሮ ታሪኮችን የጻፈችበት፤ ብራናዋ ነው ታሪኳን እና ሥልጣኔዋን የመዘገበችበት። ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ምሽግ ነው፤ ደኅንነቷን የጠበቀችበት፤ ጋሻዋ ነው ከጠላት የተከላከለችበት፤ ጦሯ ነው ጠላቶቿን ወግታ ድል የነሳችበት፤ ጸጋዋ ነው ሃብት እና ንብረት ያፈራችበት፤ ሃብቷ ነው ለሺህ ዘመናት የተጠቀመችበት፤ ገና ዘመናትም የምትጠቀምበት።

ታሪክ እና ተፈጥሮ ኢትዮጵያን እና ቀይ ባሕርን አይነጣጥላቸውም። ቀይ ባሕር ያለ ኢትዮጵያ ሙሉ ታሪክ የለውም፤ ኢትዮጵያም ያለ ቀይ ባሕር ሙሉ ታሪክ፣ ሙሉ ደኅንነት እና ማንነት ሊኖራት አይችልም። ከቀይ ባሕር ተነጥላ ልትኖር አትችልምና። ኢትዮጵያ ከባሕር ጋር የኖረች፤ ሥልጣኔዎቿን በባሕር ላይ ያደመቀች፤ ከባሕር በላይ አያሌ ታሪኮችን የሠራች ሀገር ናት፡፡ ምንም እንኳን በውጭ እና በውስጥ ጠላቶች ሴራ ለዓመታት ከቀይ ባሕር ተጠቃሚነት ብትርቅም ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር፣ ቀይ ባሕርንም ከኢትዮጵያ እስከወዲያኛው ነጥሎ ማስቀረት አይቻልም። ስለ ምን ቢሉ ኢትዮጵያ ሐቅ እና ታሪክ አላትና።

ያዕቆብ ኃይለማርያም (ዶ.ር) አሰብ የማን ናት ? በተሰኘው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያውያን ሰው ሠራሽም ኾነ ተፈጥሮ የወለዳቸውን ችግሮች በትዕግስት አሳልፈዋል። ኢትዮጵያውያን በትዕግስት የማይመለከቱት ነገር ቢኖር የድንበር መደፈርን ነው ይላሉ። ለዚያም ነው ከቀይ ባሕር ወሰን መራቃቸው የሚያንገበግባቸው። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተገነጠለች በኋላ የኢትዮጵያ ወደ ውጭ መተላለፊያ እና መግቢያ የባሕር በር መዘጋትን ያህል ኢትዮጵያውያንን ያስቆጣ እና ያሳዘነ ብሔራዊ ጉዳይ በሀገሪቱ ከቶም ተከስቶ አያውቅም ነው የሚሉት።
የኢትዮጵያ የባሕር በር መቀርቀር በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን የተፈጸመ በደል ነው። ከሁሉም የከፋ እና ተቀባይነት ከሌለው የኢሕአዴግ ፖሊሲ የኢትዮጵያን የባሕር በር አሰብን ለኤርትራ መንግሥት ማስረከቡ ነው ይላሉ። በወቅቱ ሀገር ያሥተዳድር የነበረው ሕወሃት መራሹ ኢህአዴግ የአሰብ ኢትዮጵያዊነት ወይንም አሰብ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ እና ሕጋዊ የባሕር በር መኾንዋን አይቀበልም ነበር። አሰብ የኢትዮጵያ ናት የሚሉ ቅን እና ሐቀኛ ኢትዮጵያውያንን የመስፋፋት አባዜ የተጠናወታቸው እያለ ያሸማቅቃቸው እንደነበርም ጽፈዋል።

ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን የባሕር በር ለማዘጋት በሶምሶማ ሩጫ ለድርድር ወደ አልጄርስ አቀና፡፡ አልጄርስ ከደረሰም በኋላ የባሕር በር በሚዘጉ ውሎች ተስማማ። የሚመራትን ሀገሩ በፈቃዱ ዘጋ። ኢትዮጵያን ከባሕር አርቆ አሰረ። ያለፈው አልፏል አሁን ግን የኢትዮጵያን የባሕር በር ማስመለስ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ግዴታ ነው ይላሉ። የባሕር በሮቿ በእጇ በነበሩበት ዘመን የጎለበተች እና የበለጸገች ኢትዮጵያን መመሥረት ተችሏል፡፡ በአንጻሩ የባሕር በሯን በተነጠቀችባቸው ዘመናት ኢኮኖሚዋ የኮሰሰ፤ ባሕሏ የደበዘዘ እና ፖለቲካዋ የተናጋ ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ አይተናል ነው የሚሉት።

ለአሁኑ የኢትዮጵያ ትውልድ የሚቀርበው ግልጽ ጥያቄ ኢትዮጵያ ወዳብ አልባ ኾና ኢኮኖሚዋ የኮሰሰ፣ ባሕሏ የደበዘዘ እና ፓለቲካዋ የተናጋ ኾኖ ትቀጥላለች ወይስ የባሕር በር ኖሯት ጥንት እንደነበርችው የጎለበተች እና የበለጸገች ትኾናለች? የሚለው ነው የሚሉት ጸሐፊው መልሱ አስቸኳይ ነው፡፡ ምክንያቱም በኮሰሰች እና በደበዘዘች ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ የለምና ነው ይላሉ።
ሐሪ አትክንስ የኢትዮጵያ ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ የባሕር በር በአዱሊስ እና በሌሎች እንደነበሩ ጽፈዋል። ዝነኛው እና ገናናው የኢትዮጵያ ሥልጣኔ የተገነባው፤ ኢትዮጵያ ከሌሎች ዓለማት ጋር በዲፕሎማሲ፣ በንግድ እና በሃይማኖት ስትገናኝ የኖረችው በባሕሯ በቀይ ባሕር፤ በወደቦቿ በአዱሊስ፣ በምጽዋ፣ በአሰብ በተዘረጋው ረጅሙ የባሕር ጠረፍ ነው።
ጥንታዊን ግሪኮች እና ሌሎች ሀገራት ከኢትዮጵያ በንግድ የተሳሰሩት በቀይ ባሕር ነው። ኢትዮጵያን ነገሥታት የሀገራቸውን ገናናነት የገነቡት፤ አያሌ ታሪክ የሠሩት በዚሁ በቀይ ባሕር ነው ሲሉ አትተዋል።
“የባሕሩን ታሪክ የት ይደብቁታል እንኳንስ ሰዎቹ ግምሎች ያውቁታል” እንደተባለ የቀይ ባሕር ከታሪክ ሊደበቅ አይችልም። ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ስለመኾኑ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾኑ ወርቅ እና ዝባድ እየጫኑ የሄዱ፣ ጨው እና ሌሎች የንግድ ሸቀጦችን እየጫኑ የተመለሱ የኢትዮጵያ ነጋዴ ግመሎች ያውቁታል። ዘውዴ ረታ የኤርትራ ጉዳይ በተሰኘው መጽሐፋቸው የአሁኗ ኤርትራ መረብ ምላሽ ወይም ምድሪ ሀማሴን እየተባለች በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረች የኢትዮጵያ አካል ናት፤ በዙሪያዋ ያለው የቀይ ባሕርም የኢትዮጵያ ነው ይላሉ።

ከጥንት ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ከኢትዮጵያ ወደ ተቀረው ዓለም የሚጓዙ ወገኖች መመላለሻቸው ቀይ ባሕር ነበር። የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ አክሱም በነበረበት ጊዜም ኾነ ከዚያ በኋላ በነበሩት ዘመናት የኢትዮጵያ ነገሥታት ቀይ ባሕርን እና ከዚያም እየተሻገሩ ያሥተዳድሩ ነበር ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ነገሥታት የባሕር በራቸውን ሲጠቀሙ ለዘመናት ኖረዋል። ይህም ጥቅም እስከ 1980ዎቹ ድረስ የቀጠለ ነው። አሁን ኢትዮጵያ የጠየቀችው ጥያቄ የነበረኝን ሃብቴን ስጡኝ እንጂ ያልነበረ አምጡ አላለችም።ጥያቄዋ የእውነት፣ የፍትሕ እና የሕልውና ነው። የአንድ ዘመን ብቻም አይደለም፤ የትውልድ ጥያቄ ነው እንጂ። የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ሕልውና ነው።

በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleመምህራን ለትምህርት እና ለሰላም አርበኛ በመኾን ሙያዊ ኀላፊነታቸውን መወጣት ይገባቸዋል።
Next articleየኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለቀጣናው ሰላም እና ደኅንነት መረጋገጥ ስትራቴጂካዊ ነው።