
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የጣና ሐይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን እና ሠራተኞች “ለሰላም ዘብ እንቆማለን የልማት አርበኛ እንኾናለን” በሚል መሪ መልዕክት የውይይት መድረክ አካሂደዋል።
በመድረኩ የተገኙት የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኅላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) የሰላም እጦቱ በትምህርት ዘርፉ የትውልድ ግንባታ ላይ እየደረሰ ያለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የመምህራን ድርሻ ከፍተኛ መኾኑን አንስተዋል።
መምህራን በመደበኛ መማር ማስተማር በዕውቀት ከማብቃት በተጨማሪ በመልካም ሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ የመቅረጽ ኀላፊነት አለባቸው ነው ያሉት። ተማሪዎችን በክህሎት፣ በአመለካከት እና በዕውቀት ከማብቃት ባለፈ ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል። መምህራን የትምህርት እና የሰላም አርበኛ በመኾን ሙያዊ ኀላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ነው ያስረዱት። የጣና ሐይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ፀጋዬ ተፈራ በትምህርት ቤቱ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲከናወን እና ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የጣና ሐይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ማስረሻ ተባባል ታዳጊዎች ትምህርት የሚቀስሙባቸው አካባቢዎች ሰላም ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠረው የሰላም እጦት ተፅዕኖ አሳድሯል ብለዋል።
በማስተማር ዘመናቸው ተማሪዎችን በዕውቀት ከመቅረጽ ባለፈ በሥነ ምግባር ለማነጽ ሢሠሩ መቆየታቸውን ነው ያነሱት። መምህራን ድርብርብ ሀገራዊ ኀላፊነት አለብን የሚሉት መምህሩ ስለሰላም በማስተማር ሀገር ወዳድ እና የነገዋን ኢትዮጵያ ሊገነቡ የሚችሉ ዜጎችን በማፍራት ሀገራዊ ኀላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ተናግረዋል። ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር በማድረግ የትውልድ ቅብብሎሽን ለማስቀጠል መምህራን፣ ወላጆች፣ ማኅበረሰቡ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸውም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
