
ባሕርዳር፡ የካቲት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጭቃ ተሽከርካሪ ሠርተን፣ ሽቦ ጠምዝዘን እንደመኪና እየነዳን፣ አባሮሽ ተጫውተን፣ ታላላቆቻችንን አክብረን ወንበር ለቀን አስቀምጠን፣ ጉልበት ስመን እና ለጎረቤት ታዝዘን ማደግ የብዙዎቻችን ኢትዮጽያውያን ትዝታ ነው። ይህ አስተዳደግ የመለወጥ ፍላጎታችን እና ለቴከቴክኖሎጅም ያለንን ጥማት አንዱ ማሳያ ነው።
መተባበር እና መደጋገፍን በማኅበረሰቡ አማካኝነት ወደ ውስጣችን አስርጸንም ነው ብዙዎቻችን ስናድግ። ይህን የልጅነት ጊዜ እንድናነሳ ያነሳሳን በመንገድ ላይ ሕጻናት በኮባ፣ በጣውላ እና በካርቶን የጦር መሣሪያ ሠርተው “ገደልኩህ፤ አጠፋውህ” ሲሉ በመታዘባችን ነው። ሕጻናት በአንድ ኾነው ስለ መገዳደል፣ አንዱን ስለመጥላት እና ሌላውን ስለመውደድ፣ ከሀገራቸው ፍቅር ይልቅ በውጭ ሀገር ስለመኖር እያነሱ ሲጫወቱ ማየት የተለመደ ትዝብት እየኾነ ነው።
ሕጻናት በልጅነት አንደበታቸው ስለመገዳደል ተግባራዊ ልምምድ ያደርጋሉ፤ እንደ ሠራዊት በሰልፍ እየተጓዙ የጦርነት ልምምድ ያደርጋሉ። ይህ እንዴት ሊኾን ቻለ፤ ትውልዱ ወዴት እያመራ ይኾን፤ ምን ይገጥመንስ ይኾን? የሚሉ ጥያቄዎቸን መልስ ፍለጋ በሃሳብ መጓዝ ግድ ይላል። እዚህም እዚያም የሚፈጠሩ ግጭቶች በሕጻናት የሥነ አዕምሮ ዕድገት እና ፍላጎት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ስለመኾኑ ምልክቶች እየታዩ ነው። የእንጅባራ ዩኒቨርስቲ አሥተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት እና ዕድገታዊ ሥነ ባሕሪ (ሳይኮሎጅ) መምህር እና ተመራማሪ ወሃቤ ብርሃን (ዶ.ር) ሕጻናት የሚያድጉበት አካባቢ እና ሁኔታ ለአወንታዊ እና አሉታዊ አመለካከታቸው ወሳኝነት እንዳለው ይገልጻሉ።
ሕጻናት ጥሩም ኾነ መጥፎ አመለካከትን የመቅሰም ክህሎታቸው ከፍተኛ መኾኑን አንስተዋል። ሕጻናት አዎንታዊ አመለካከት ካለው ማኅበረሰብ መልካምነትን፤ መረዳዳት እና አብሮነትን እንደሚማሩ ይናገራሉ። ለአሉታዊ ድርጊቶች በተጋለጡ አካባቢዎች ሲያድጉ ደግሞ ስርቆት፣ ሱስ፣ ጦርነት እና ሌሎች ድርጊቶችን በሕይወታቸው እንደሚማሩ እና በተግባርም እንደሚገልጹ አንስተዋል። ግጭት በሚከሰትበት አካባቢ የሚኖሩ ሕጻናት ጠብ አጫሪነትን እና መገዳደልን ተላምደው እንደሚያድጉ ነው ያስረዱት። ልጆች በመልካም ባሕሪ ካልታነጹ አብሮነትን፣ መተባበርን እና የሀገር ፍቅርን መገንዘብ ስለማይችሉ በሀገር ተተኪ ትውልድ ላይ የሚያደርሰው ኪሳራ ከፍተኛ መኾኑንም አንስተዋል።
ሕጻናት ነገሮችን የማመዛዘን አቅማቸው አነስተኛ በመኾኑ ሥነ ልቦናቸውን፣ ባሕሪያቸውን እና አመለካከታቸውን በመልካም ተግባር ከመቅረጽ አንጻር ወላጆች እና ማኅበረሰቡ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ተመራማሪው መክረዋል።
ልጆች በማኅበራዊ ሚዲያ የሚመለከቷቸውን ነገሮች መከታተል ብሎም ግብረ ገብነት፣ መተሳሰብ፣ መደጋገፍ እና ትምህርት ሰጭ የኾኑ ይዘቶችን እንዲከታተሉ ማድረግ ከወላጆች የሚጠበቅ ተግባር መኾኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የተማሪ ወላጆች ምክትል ፕሬዝዳንት አዱኛ እሽቴ ወላጆች እንደ ሃይማኖታቸው አስተምሮ ልጆቻቸውን በሥነ ምግባር በማነጽ የሀገር ፍቅርን ማስተማር እና አብሮነትን በሥነ ልቦናቸው ማሳደር ያስፈልጋል ብሏል። ከወላጆች ባሻገር ማኅበረሰቡ ባሕላዊ እሴቶችን እና መቻቻልን በማስተማር በጎ ሀገር ተረካቢ እንዲኾኑ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል። ከግጭት እና ጦርነት በመውጣት ልጆች መልካም ነገሮችን ተምረው የሚያድጉባት ሀገር መገንባት እንደሚያስፈልግም መክረዋል።
ልጆች የቀጣዩን ዘመን የሚዋጁ ቴክኖሎጂዎችን እየተለማመዱ እንዲያድጉ ወላጆች ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም መልእክት አስተላልፈዋል። ተወዳዳሪ የማያደርጉ ድርጊቶችን እንዳይለማመዱም ወላጆች ክትትል የማድረግ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የተጠቀምነው ምስል በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተዘጋጀ ነው።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
