ለውጥ ያመጡ የግብርና ምርምር ሥራዎች እየተሠሩ ነው።

8
ባሕርዳር፡ የካቲት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስተባባሪነት ዓመታዊ ክልላዊ የምርምር ሥራዎች ግምገማ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ በክልሉ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ በምርምር የተገኙ ውጤቶች፣ በምርምር ዘርፉ የተገኙ ጥናቶች፣ በቀጣይ መሠራት ባለባቸው ጉዳዮች፣ በዘርፉ ዕድገት እና ውጤታማነት ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች እና የመፍትሔ ሃሳቦች ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።
የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰማኝ አስረዴ ( ዶ.ር ) የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በሀገር አቀፍ ደረጃ የበግ ዝርያን እና በድንች ዝርያ ማሻሻል ላይ ምርምሮችን እንደሚያስተባብር ገልጸዋል። በክልል ደረጃ ደግሞ አጠቃላይ የግብርና ምርምርሮችን በኀላፊነት እየመራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም በሰብል፣ በእንስሳሳት፣ በአፈር እና ውኃ፣ በደን፣ በምግብ ሳይንስ፣ በዘር እና በባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ ምርምሮችን በማካሄድ በርካታ ውጤቶችን ማውጣቱን ነው የገለጹት። ባለፈው ዓመትም 470 የሚደርሱ ምርምሮች ተካሂደው 97 የሚኾኑ ውጤቶች መውጣታቸውን ጠቅሰዋል።
ቁጥራቸው 960 የሚኾኑ የምርምር ሥራዎች ደግሞ በዚህ ዓመት ለግምገማ ይቀርባሉ ነው ያሉት። ከዚህ ውስጥም 351 የሚኾኑት አዲስ እንደኾኑ እና 371 የሚኾኑት ይጠናቀቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አንስተዋል።
የምርምር ሥራዎች ከተጠናቀቁ በኋላም በሌላ ፎረም ወደ አርሶአደሮች መሄድ መቻል እና አለመቻላቸው ተጣርቶ ወደ ቴክኖሎጂ እንደሚሄዱ ገልጸዋል። ዛሬ የጀመረው እና ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቆየው መድረክ ግን የሚጸድቁትን ለመወሰን በቂ አለመኾኑን አስገንዝበዋል።
የደብረብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ደጉ ተመሥገን የተጠቃሚውን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ቴክኖሎጂ ማውጣት፣ ማስተዋወቅ እና የወጣውን መነሻ ዘር መስጠት ላይ ሥራዎችን እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል። አሁን ላይ በመንዝ በግ መረጣ እና በማሻሻል አርሶአደሮች ላይ ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ያመጣ ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል። የወተት ምርትን የሚያሻሽሉ ሥራዎችን እየሠሩ መኾናቸውንም አንስተዋል።
ለአካባቢው አርሶአደሮች የእንስሳት ምርት ዋና የኢኮኖሚ መሠረት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ አርሶ አደሮች የሚወጡ ቴክኖሎጅዎችን ፈልገው እንደሚወስዷቸው እና እየተጠቀሙባቸው እንደኾነም ገልጸዋል።
በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ዋና ጸሐፊ ተወካይ ጀጃው ደማሙ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲዎች በማኅበረሰብ አገልግሎት እና ምርምር ዘርፍ የተለያዩ ተልዕኮዎች ተሰጥተዋቸው ሥራዎችን በቅንጅት እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል። የኅብረተሰቡን ኑሮ ለመቀየር የሚያስችሉ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ እንደኾነም አንስተዋል። በዚህም ለውጥ እየመጣ እንደኾነ ነው የጠቀሱት። የሚቀሩ ሥራዎች ግን አሉ ብለዋል።
በቀጣይም በምርምር ሥራዎች ላይ ዩኒቨርሲቲዎች ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየባሕር በር የትውልድ ሕልውና ነው።