
ባሕርዳር፡ የካቲት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የድርማ መስኖ ፕሮጀክት በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ 035 ቀበሌ እየተገነባ የሚገኝ ነው። በስድስት ወራት ውስጥ ግንባታው 85 በመቶ ደርሷል፡፡
የቃሉ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሳኒ ሙሐመድ የድርማ መስኖ ፕሮጀክት በባሕላዊ መስኖ ሲያከናውኑ የነበረውን የግብርና ሥራ ወደ ዘመናዊ አሠራር የሚቀይር መኾኑን ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ወንዝን በባሕላዊ መንገድ የመጥለፍ ድካምን ያስቀራል ነው ያሉት፡፡
የግድቡ ሥራ ሲጠናቀቅ በርካታ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አንስተዋል። በዓመት እስከ ሦሥት ጊዜ ማምረት እንደሚያስችላቸውም ተናግረዋል፡፡ አካባቢው ለአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ምቹ በመኾኑ አርሶ አደሮችን ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡
ማኅበረሰቡም ደስተኛ መኾኑን እና ለፕሮጀክቱ ስኬት ትብብር እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
የቃሉ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ መርሐግብር መሐንዲስ መሐመድ መኮንን የድርማ መስኖ ፕሮጀክት በነሐሴ/2017 ዓ.ም ውል ተወስዶ በመስከረም/2018 ዓ.ም ወር ወደ ግንባታ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በ16 ወራት ጊዜ ለማጠናቀቅ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱን የሚገነባው ኤፍ.ቲ.ኤን. ኮንስትራክሽን ነው፤ ድርጅቱ ባለፉት ሰባት ወራት ግንባታውን በጥሩ ኹኔታ በማከናወኑ አፈጻጸሙ 85 በመቶ ደርሷል ነው ያሉት፡፡ ፕሮጀክቱ የተሻለ አፈጻጸም ያለው በመኾኑ ለሌሎችም ፕሮጀክቶች ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው ብለዋል፡፡
የአካባቢው ሰላም መኾን፣ የማኅበረሰቡ ተባባሪነት፣ ተቋራጩ ለሥራው ያለው ቁርጠኝነት እና አስፈላጊ የኾኑ የሰው ኀይል እና ማሽነሪዎችን በማስገባት ጊዜውን በአግባቡ መጠቀሙ ፕሮጀክቱ ጥሩ አፈጻጸም እንዲኖረው እንዳደረገ ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ 5 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የመዳረሻ የጠጠር መንገድ፣ 250 ሜትር በላይ የኾኑ ሁለት የውኃ መጥለፊያ መስመሮች፣ 483 ሜትር ካናሉ እንዳይሸረሸር የመከላከያ ግንብ እና 5 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ዋና ካናል ተሠርተዋል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከ290 ሄክታር በላይ መሬት በማልማት 366 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ በግንባታው ላይ እስካሁን ችግር እንዳላጋጠመ የገለጹት መሐንዲሱ ከታቀደለት ጊዜ ቀደም ብሎ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
በጀትን፣ የሰው ኀይልን፣ ጥሬ እቃን እና ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ፕሮጀክቶችን በታቀደላቸው ጊዜ መሥራት እንደሚቻል ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የመስኖ እና ድሬኔጅ ግንባታ ክትትል ዳይሬክተር ጌትነት አያሌው የድርማ መስኖ ፕሮጀክት በ357 ሚሊዮን ብር በጀት የሚገነባ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ የበጀት ምንጩ የዓለም ባንክ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም መኾኑንም ነው የገለጹት፡፡
ፕሮጀክቱ በፍጥነት እየተገነባ መኾኑን አንስተዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብም ለመስኖ ሥራው ተባባሪ ኾኖ የሦሥተኛ ወገን ችግሮችን በመፍታት እና የወረዳ አሥተዳደሩ ተቋራጭ የሚያጋጥሙትን ችግሮች በፍጥነት መፍታቱ አስተዋጽኦው ከፍተኛ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ለአርሶ አደሮች ሰፊ መሬት ያለማል፣ የአርሶ አደሮችን ድካም በመቀነስ በዓመት እስከ ሦሥት ጊዜ ለማምረት ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡ ይህም ምርት እና ምርታማነትን በመጨመር አርሶ አደሮችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ክልል የመስኖ ፕሮጀክቶች መጓተት እንዳለ ያነሱት ዳይሬክተሩ ለዚህም ዋናው ምክንያት የጸጥታ ችግር መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዓመት 135 ፕሮጀክቶችን ወደ ግንባታ በማስገባት 88ቱን ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሠራ እንደኾነም አስገንዝበዋል። በስድስት ወራት ውስጥም 75 ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ ገብተው 17 ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
