
ባሕርዳር፡ የካቲት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢ ጠህናን ወረዳ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረገው የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ተፈታኝ ተማሪ ለፈተና ዝግጅት እያደረገ መኾኑን ገልጿል።
በፈተናው የተሻለ ውጤት ለማምጣት መምህራን ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ ከጓደኞቹ ጋር በመረዳዳት ጠንክሮ እያነበበ መኾኑን ተናግሯል።
ወላጆቹም አጋዥ መጽሐፍ በመግዛት ድጋፍ እንዳደረጉለትም ገልጿል። በፈተናው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብም አቅዷል። ሌሎች ተማሪዎችም ጊዜአቸውን በአግባቡ በመጠቀም ለፈተናው ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለባቸው ተናግሯል።
በጃቢ ጠህናን ወረዳ የአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር እንደገለጹት ባለፈው ዓመት በወቅታዊ ችግሩ ምክንያት በትምህርት ቤቱ ክልል አቀፍ ፈተና አልተሰጠም። ተማሪዎችም ለሁለት ዓመታት ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው መቆየታቸውን ነው ያነሱት።
እነዚህን ተማሪዎች በፈተናው ውጤታማ ለማድረግ መምህራን የሥነ ልቦና ግንባታ ከመሥራት ባለፈ ልዩ ድጋፍ እየሰጡ ነው ብለዋል። ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኅላፊ የስጋት ደሴ በዞኑ በ2018 የትምህርት ዘመን 4ሺህ 634 የ6ኛ እና 5ሺህ144 የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች የክልል አቀፍ ፈተና እንደሚወስዱ ገልጸዋል። በሀገር አቀፍ ፈተናም 3ሺህ 376 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ይፈተናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የተናገሩት።
የጸጥታ ችግሩ ተፅዕኖ ቢኖረውም ተፈታኝ ተማሪዎችን በሚሰጠው ፈተና የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ቅዳሜ እና እሑዱን ጨምሮ የማካካሻ ትምህርት በትኩረት እየተሰጠ ነው ብለዋል።
በትምህርት ቤቶችም ተማሪዎቹ የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት እንዲያነኙ ተደርጓል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኅላፊ ጥላሁን ወርቅነህ የክልሉ ተማሪዎችን ለማብቃት በትምህርት ቤቶች የመጻሕፍት ግብዓት ማሟላት እና የአዳር ጥናት እንዲካሄድ እየተደረገ ነው ብለዋል። በዚህም በሀገር አቀፍ እና ክልል አቀፍ ተፈታኝ ተማሪዎች ብቁ እና ተወዳዳሪ ኾነው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ጥረት እየተደረገ መኾኑን አስገንዝበዋል።
ተማሪዎች የሚጠበቅባቸውን ዕወቀት ቀስመው በሚሰጠው ፈተና የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የትምህርት ባለ ድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
