የምርምር ውጤት ከጽሑፍ ባሻገር ወደ እርሻ ማሳ መውረድ አለበት።

4
ባሕርዳር፡ የካቲት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስተባባሪነት ዓመታዊ ክልላዊ የምርምር ሥራዎች ግምገማ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ በክልሉ ከሚገኙ የምርምር ማዕከላት እና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ተመራማሪዎች፣ የግብርና ልማት አጋር አካላት፣ በሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ የግብርና ምርምር ሥርዓት ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ተመራማሪዎች እና የሥራ ኀላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ ግብርናን ከኋላ ቀርነት አውጥቶ ዘመናዊ እና የኢንዱስትሪ መሠረት ለማድረግ የሚደረገው ጉዞ ያለ ምርምር እና ሳይንሳዊ ግኝት ሊታሰብ እንደማይችል ተናግረዋል።
ምርምር ለኛ ምርጫ ሳይኾን የሕልውናችን ዋስትና፣ የልማታችን መሪ ኮምፓስ እና ወደ ብልጽግና የሚወስደን ሞተራችን ነውም ብለዋል፡፡
ክልሉ በተፈጥሮ ጸጋዎች የታደለ ነው ያሉት ኀላፊው ጸጋ ወደ ብልጽግና የሚቀየረው በዕውቀት፣ በቁርጠኝነት እና በትጋት ተቀናጅቶ መሥራት ሲቻል እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ተግባራዊነቱ ደግሞ በተመራማሪዎች የቴክኖሎጂ ፈጠራ ቀዳሚነት፣ በምሁራን እና በሁሉም ተባባሪ ባለድርሻ አካላት እጅ ላይ እንዳለ ነው የጠቀሱት።
ተመራማሪዎች የሚያካሂዱት ምርምር ከተግባራዊ ችግሮች የሚጀምር፣ ወደ ተግባር የሚደርስ እና ለሕዝብ ጥቅም የሚውል መኾን እንዳለበትም አንስተዋል። የምርምር ውጤት ከጽሑፍ ባሻገር ወደ እርሻ ማሳ መውረድ እና ከላቦራቶሪ ወደ አርሶ አደር እርሻ መድረስ አለበት ብለዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰማኝ አስረዴ (ዶ.ር) ክልሉ በሰላም ማጣት ምክንያት ከውጭ በሚገቡ እና ከየአካባቢው በሚመጡ ሸቀጦች ዋጋ መጨመር፣ በግብዓት እጥረት እና በዋጋ መዋዠቅ እየተፈተነ መኾኑን ተናግረዋል።
ለእነዚህ አብዛኛዎቹ ችግሮች ዋና መንስኤው የክልሉ የግብር ኢኮኖሚ የዕለት ከዕለት እርሻ ላይ በእጅጉ ጥገኛ መኾን እና በግብርና ዘርፍ ዝቅተኛ አፈጻጸም መኖር እንደኾነም ጠቁመዋል።
ለዚህም የተሻሻለ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን አቅርቦት እና አጠቃቀም በመጠቀም መቅረፍ እንደሚያስፈልግ ነው ያስገነዘቡት።
የግብርና ምርትን እና ምርታማነትን የማሳደግ ተግባር በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ዋና ዋና የግብርና ዘርፍ የልማት ስትራቴጂዎች አንዱ እንደኾነም አንስተዋል።
በመድረኩ በክልሉ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ በምርምር የተገኙ ውጤቶች፣ በምርምር ዘርፉ የተገኙ ጥናቶች፣ በቀጣይ መሠራት ባለባቸው እና በዘርፉ ዕድገት እና ውጤታማነት እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች እና የመፍትሔ ሃሳቦች ላይ ውይይት ይደረጋል ነው የተባለው።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleወጣቶች ለሀገር ሰላም የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይገባቸዋል።
Next articleየሀገር አቀፍ እና ክልል አቀፍ ተፈታኝ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እየተሠራ ነው።