በጎነት ከሕግ ሳይኾን ከሕሌና የሚመነጭ የመንፈስ እርካታ ነው።

13

 

ባሕርዳር፡ የካቲት 29/2018ዓ.ም(አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ደብረ ጽዮን ሰላም አርጊው ማርያም ገዳም የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት “መፃጉን” ምክንያት በማድረግ ከ6ሺህ በላይ ለሚኾኑ አቅመ ደካሞች እና የጎዳና ተዳዳሪዎች የሕክምና ምርመራ፣ የመድኃኒት፣ የጽዳት እና የአልባሳት ድጋፍ አድርጋለች።

የደብረ ጽዮን ሰላም አርጊው ማርያም ገዳም አሥተዳዳሪ መላከ ጽዮን አባ ገብረ ሚካኤል ድረስ ረዳት ያልነበረው “መፃጉ” ለ38 ዓመት ያልጋ ቁራኛ ኾኖ የቆየ መኾኑ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ሲመጣ ከበሽታው በቃሉ እንደፈወሰው ለማስታወስ ሲባል ለአቅመ ደካሞች የድጋፍ መርሐ ግብሩ መካሄዱን አስረድተዋል።

በዚህም በተለይም አቅመ ደካሞች የሕክምና አገልግሎት እና ሌሎችን ድጋፎች እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

መርሐ ግብሩ በዚህ ዓመት ለ8ተኛ ጊዜ መከናወኑን ነው የተናገሩት።

የቤተክርስቲያኒቱ የበጎ አድራጎት እና ሥነ ምግባር አስተባባሪ በኩረ ትጉሀን ቄስ ማንደፍሮ ካሴ ድጋፉ ከተለያዩ የግል እና የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም ከማኅበረሰቡ መሠብሠቡን ተናግረዋል።

በመርሐ ግብሩ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጡ ያገኘናቸው በፈለገ ሕይወት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የማኅበረሰብ ጤና ባለሙያው ፀጋዬ አድማስ በዕለቱ የሕክምና ባለሙያዎች በሙያቸው በጎነትን ለመግለጽ የድርሻቸውን እየተወጡ መኾኑን ተናግረዋል።

በጎነት በሕግ የሚመራ ሳይኾን ከሕሌና የሚመነጭ እና የመንፈስ እርካታ ያለው መኾኑን ገልጸው ሌሎችም የድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በተደረገው የበጎ ተግባር ስምሪት ሲታገዙ ያገኘናቸው እማሆይ ፀጋነሽ ይርዳው ሕመማቸውን የሚያሳክም ረዳት እንዳልነበራቸው ነግረውናል።

በተደረገላቸው የሕክምና ድጋፍ ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸው ምስጋናም አቅርበዋል። ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleብርቱዋ ሴት
Next articleብሔራዊ ጥቅም የሀገር ሕልውና መሪ ኮምፓስ ነው።