
ባሕርዳር፡ የካቲት 29/2018ዓ.ም(አሚኮ) ሴትነት ውበት፣ ሴትነት ክብር፣ ሴትነት ከአምላክ የተሠጠ ድንቅ ጸጋ ነው።
ሴትነት በአስተዋይነት ቤትን እና ሀገርን የመምራት ጥበብ እና ብርታት ነው። ዛሬ ደግሞ የሴቶች ቀን ናት። ይቺን ቀን ደግሞ በዋዛ ማለፍ አልፈለግሁምና አንድ ትዝብቴን ላካፍላችሁ ወደድኩ። አሁን ላይ ከምሠራበት ተቋም ውጭ ሌላ ሁለት ተቋም ላይ ሠርቻለሁ። በዚህ ሂደት በርካታ ሰዎችን የማወቅ ዕድል ገጥሞኛል። ይበልጥ ደግሞ ሴቶችን።
ብዙ ጊዜ መደበኛ ሥራችን ከውነን ሻይ እየጠጣን ፋታ ለመውሰድ፤ አንዳንድ ጊዜም ምሳ ለመብላት ስንገናኝ ከሥራ ያለፉ የግል ጉዳዮቻችን እንጨዋወታለን።
ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት የሥራ ባልደረባየ እንደተለመደው ምሳ እየበላን “ምን እንደናፈቀኝ ታውቃላችሁ” አለችን። ለመስማት በመጓጓት እና እሽ ቀጥይ በሚል ዓይነት ዕይታ ሁላችንም ለማዳመጥ ቀና አልን። ሥራ ስኾን ልጆቼን የምትንከባከብልኝ፤ ሲኾንም የቤት ውስጥ ሥራዎችን የምታግዘኝ አጋዥ ማግኘት አለችን።
እኔም ከሚከፈልበት ይልቅ የማይከፈልበትን አድካሚ የሥራ ውጣውረድን እረዳለሁና አጋዥ የለሽም አልኳት። አወ፤ ብፈልግ ባስፈልግ ላገኝ አልቻልኩም፤ በደላላ ሞክሬ ነበር፤ የድለላ ገንዘብ ለማግኘት ደውሎ ብዙ ሳትቆይ ወሰደብኝ አለችኝ። እና በሌላ ደላላ አልሞከርሽም አልኳት። አይ በሚል አግራሞት የተዋዛ ሀሳቧን ቀጠለች።
አንድ ጊዜ ብቻ መስሎሽ ነው? ሁለት ሦሥት ጊዜ ነው ይህ የኾነው፤ ከዛ በኋላ በደላላ የሚመጣ አጋዥ ለማስገባት እምነት አጣሁ አለችኝ።
የቤቱን ሥራ እንዴት እያደረግሽ ነው ታዲያ ? አልኳት። ላያስችል አይሰጥም ብላ ያለባትን ውጣ ውረድ በውስጧ አፍና ፈገግ በማለት ሀሳቧን ቀጠለች። ሦሥቱም ልጆቿ ለትምህርት በመድረሳቸው እና ቤት ውስጥ የሚውል የግድ ሰው የሚያስፈልገው ሕጻን ባለመኖሩም ፈጣሪዋን አመሰገነች። ከሁሉም በላይ ግን ለአንድ ቀን ያለ ጭንቀት በጊዜ መተኛትን እና እንደማንኛውም ሰው ከጨለማ እና ከእንቅልፍ ጋር ሳትጋፋ ሲነጋ ጋደም ካለችበት አልጋዋ ቀና ማለትን ተመኘች።
ለሙሉ ቤተሰቡ ቁርስ እና የሚቋጠር ምሳ ለመሥራት ከንጋቱ 10:00 እንደምትነሳም ነገረችኝ። አንዱ ሲያልቅ ሌላው የሚተካውን የቤት ውስጥ ሥራ ስትጨርስ የጠዋት ጮራ አብራ እንደምትፈነጥቅም አነሳች። ከዚያም ልጆቿን ከእንቅልፍ ቀስቅሳ ቁርስ አብልታ ሰዓት ካላት እርሷም በልታ ደግሞም እንደ ሥራ ጓደኞቿ እራሷን ጠብቃ ወደሥራዋ ለመምጣት እንደምትዘጋጅ ነገረችኝ።
አቤት የጥዋቱ ሰዓት ፍጥነቱ በዛ ላይ ብሉ አትብሉ ከልጆቼ ጋር የምለማመነው እና የምፈጀው ጊዜስ አለች የዘወትር ማለዳዋን ስትነግረኝ።
ይህች የሥራ ባለደረባየ በዛ ሁሉ ወከባ አልፋ እንደማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ የሥራ ሰዓቷን አክብራ እና ራሷን ጠብቃ ነበር ቢሮ የምትገኘው። ምን አልባት ልጆችን ትምህርት ቤት የሚወስድላት የትምህርት ቤቱ ተሽከርካሪ ከቀረ ልጆቹን ትምህርት ቤት ለማድረስ ትዘገይ ይኾናል እንጂ በሥራዋ ታታሪ ናት። አንዳንድ ቀን ግን ድካሟ ፊቷ ላይ ያሳብቃል።
ቀኑን እንደዚህ አልፋ የልጆቿ ከትምህርት ቤት መውጫ ሰዓት ሲደርስ ልጆቿ ወደ ቤት መመለሳቸው ያስጨንቃታል። አንዳንዴ ለአከራዮቿ ደውላ ትጠይቃለች። ቤት መድረሳቸውን ስታረጋግጥ አዕምሮዋ እርፍ ያለ ይመስላል።
የቢሮ ሥራዋን ከውና ወደቤቷ ስትመለስ ብዙ ጊዜ እያሰበች የምትሄደው ቤት የምትሠራውን ሥራ እንደኾነም ነግራኛለች። ልጆቿ በዕድሜያቸው ገና ትንንሾች ናቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞም በእርስ በእርስ የቀልድ ድብድብ እና ጨዋታ ጠዋት ያስተካከለችው ቤት ተፈላልሶ፣ ጠዋት የቀረው ያልታጠበ እቃ፣ መክሰስ የተበላበት እና ምሳ የተቋጠረበት እቃ ተከማችቶ የእርሷን እጅ ለአጠባ እንደሚጠብቅም በሀሳብ ልውውጣችን ተረድቻለሁ።
ምሽቱም ለእርሷ እረፍት አልባ ነው። የምሽቱ ሥራ ይደር እንዳትል ለጥዋቱ ሥራ ሌላ ጫና ነው። አንዳንድ ቀን ደግሞ ምሽቱ ልብስ በማጠብ ሊታጀብ ይችላል።
ይህ ሲኾን የትዳር አጋሯስ ካላችሁ ብዙ ጊዜ ለሥራ የሚንቀሳቀስ ዓይነት ሰው ነው።
እንደ ቀድሞ የሥራ ባለደረባየ ዓይነት ስንት ብርቱ ሴቶች ይኖሩ ይኾን? የሴቶችን ቀን ስናስብ የሴቷን ድካም፣ ጥንካሬዋን እና አለኝታዋን እናስብ። እናክብራት፤ እንውደዳት፤ እናግዛት። ራሷን የምትሰጠው ለትውልድ፣ ለሀገር እና ለነገ ተስፋ ነውና።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
