ወጣቶች ሀገራዊ አመለካከት እንዲኖራቸው እየተሠራ ነው።

16

 

ባሕርዳር፡ የካቲት 29/2018ዓ.ም(አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር “ለሰላም ዘብ እንቆማለን፤ የልማት አርበኛ እንኾናለን” በሚል መሪ መልዕክት ከሲቪክ ማኅበራት እና ከወጣት አደረጃጀቶች ጋር ውይይት አድርጓል።

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ ወጣቶች የነገ ሀገር መሪ እና ተረካቢ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ወጣቶች ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን በሚመለከት የተስተካከለ ዕውቅና እንዲኖራቸው ያስፈልጋል ብለዋል። ለዚህም በተለያዩ አጋጣሚዎች የማወያየት ሥራ እየተከናወነ እንደኾነ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ጠላቶች የማኅበራዊ ሚዲያ መበራከትን እንደ ዕድል ተጠቅመው ሀገር ለማፍረስ እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። ወጣቶችን በተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ መጠቀሚያ እያደረጉ እና ለችግር እየዳረጓቸው መኾናቸውን ጠቁመዋል።

ለወጣቶች የጠላትን ሴራ ማስገንዘብ እና በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መረጃዎችን መርጠው መጠቀም እንዲችሉ በማድረግ የተስተካከለ ሀገራዊ አመለካከት እንዲኖራቸው እየተሠራ ነው ብለዋል።

ሰላም እና ልማትን ለማደናቀፍ የሚሠሩ አካላትን መከተል እንደሌለባቸውም አሳስበዋል።

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ገንዘብ መምሪያ ኀላፊ አጸደ ምንዋጋው ወጣቶች በተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ መታለል እንደሌለባቸው አስገንዝበዋል። ሀገር ለማፍረስ የሚሠሩ በርካታ አካላት መኖራቸውንም መገንዘብ እንደሚገባ አንስተዋል።

ወጣቶች ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ መሥራት አለባቸው ብለዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ ወጣቶችም መድረኩ ስለ ክልላዊ እና ሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። በውይይቱ ለሰላም ከመቸውም ጊዜ በላይ መሥራት እንዳለብን ተገንዝበናል ነው ያሉት።

የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እና ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

ዘጋቢ ፦ አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእስከመቼ ነው ?
Next articleብርቱዋ ሴት