እስከመቼ ነው ?

29

ባሕር ዳር: የካቲት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በወቅቱ
ጎንደር ከተማ እኖር ነበር። በወርሐ ጥር 2018 ዓ.ም ወደ ባሕር ዳር የሚያስሄድ አንድ ጠንካራ ማኅበራዊ ጉዳይ ገጥሞኛል። ነገር ግን የመንገዱ ጉዳይ ዳገት ኾኖብኛል። በአውሮፕላን መጓዝን እንደ አማራጭ ለመጠቀም ባስብም ከጎንደር ባሕር ዳር በቀኑ በረራ አይደረግም። በአዲስ አበባ ዞሮ ለመሄድ ደግሞ የሚቻል አልኾነም። በዚህ መካከል የምሄድበት ማኅበራዊ ጉዳይ ሊያልፈኝ ኾነ።

አሁን በየብስ ትራንስፖርት መጓዝ ግዴታ ኾነብኝ። በአማራ ክልል ግጭት ከተፈጠረ ጀምሮ መንገዶች ሁሉ አስተማማኝ አይደሉም። ይህ ደግሞ ታላቅ ስጋት ነው።
ስለ ምን ቢሉ መንገድ ላይ እገታ እና ዘረፋ አለና። ብታገት በእኔ ላይ ከሚደርሰው ችግር ባለፈ ለቤተሰብ እዳ መኾንን ፈራሁ። እኔም በታጣቂዎች ተይዤ ዋጋ መክፈል የለብኝም።

ኾኖም መሄዴ ግድ ኾነብኝ። ረቡዕ ማለዳ አዘዞ መናኽሪያ ተገኝሁ። መናኽሪያ እንደተለመደው በተጓዦች ተጨናንቃለች። መኪና ውስጥ ገብቸ ተቀመጥኩኝ፤ ቀስ በቀስ መኪናው በተጓዦች ተሞላ።

ከመናኽሪያ ወጥተን ጉዞ ተጀመረ። ጠዳ ከተማን ካለፍን በኋላ የታጣቂ ኃይሎችን በመስጋት ሁሉም ስልኩን እና የእጅ ሰዓቱን መደበቅ ጀመረ። ስጋት፣ ጭንቀት እና ፍርሃት በሁሉም ልቦና ውስጥ አደረ። አሽከርካሪው ከባሕር ዳር ጎንደር የሚመጡ አሽከርካሪዎችን በመስኮት በኩል “መንገድ ሰላም ነው” እያለ ይጠይቃል። ሰላም ነው አይዟችሁ የሚል ምላሽም ሲሰጡትም ሰማሁ።

በዚህ መልስ እኔን ጨምሮ ሁሉም መንገደኞች በመጠኑ መረጋጋት አሳየን። በዚህ ጊዜ ነበር ከጎኔ ከተቀመጠው ወጣት ጋር ማውራት የጀመርነው። ጥቁር የሀዘን ኮፊያን አድርጓል።

ሰላምታ ተለዋወጥን። ምን አጋጥሞህ ነው ጥቁር የለበስከው ? አልኩት። በሃዘን ውስጥ ኾኖ እናቱን በሞት እንዳጣ ነገረኝ። ታመው ነበር? ቀብረህ እየተመለስከ ነው? ጥያቄዬን አከታተልኩበት።

የገጠመውን ያጫውተኝ ጀመር። እናቱን ለማስታመም ከባሕር ዳር ወደ ጎንደር በሚጓዝበት ወቅት በአጋጣሚ ከታጣቂዎች እጅ ወደቀ። መታወቂያው ሲታይ የመንግሥት ሠራተኛ በመኾኑ ከመኪና እንዲወርድ ተደረገ። ታጣቂዎችን እናቱን ለማስታመም እየሄደ መኾኑን እየነገረ ቢማጸናቸውም ሊራሩለት እንዳልፈቀዱ ነገረኝ። አግተው ወደ ጫካ በመውሰድ ለቤተሰቡ ደውለው አንድ ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ ጠየቁ። ገንዘቡ ካልተከፈለ ቀጥሎ የሚመጣው ሞት ነው።

አንድ ሳምንት ከታጣቂዎች ጋር በፍርሃት እና በጭንቀት ቆየ። ከማኅበረሰቡ ተለምኖ አንድ ሚሊዮን ብር ለታጣቂዎች ከተከፈለ በኃላ ተለቀቀ።

እናቱን ለማየት፣ አግኝቶ ለማስታመም ቸኩሏል። ዳሩ ያሰበው አልኾነም። ወደ እናቱ ቤት ሲደርስ እናት ልጇን ለሦስት ዓመታት ማየት እንደተመኘች፤ አቅፋ መሳም የልጅነት ጠረኑን ማሽተት እንደናፈቀች በሞት ተለይታ ነበር። በዚህም ምክንያት ሀዘኑ ከባድ እንደኾነ ዓይኖቹ እንባ እያቀረሩ ነገረኝ።

እናቱን ባለማስታመሙ፤ ወደ ሕክምና ባለማድረሱ፤ የእናቱ እቅፍ፤ የእናቱ ጉርሻ እንደናፈቀው፤ እሷን መጦር ውለታዋን በእንክብካቤ ለመመለስ እንደደረሰላት ሳይነግራት፤ የልጇን የድካሟን ፍሬ፣ ወግ፤ ማዕረግ ሳታይ በሞት በመለየቷ የእግር እሳት ኾኖ እየለበለበው መኾኑን በሃዘን ስሜት ነገረኝ።

ሰላም ቢኾን ኖሮ እናቱ ከመሞቷ በፊት ሊደርስ ይችል ነበር። ይህ አለመኾኑ ልቡን ሰብሮታል። የገጠመው ነገር የማይፋቅ የአዕምሮ ቁስል እንደኾነበትም አነሳልኝ። እርሱ ይሄን ታሪክ እየነገረኝ ዛሬስ መንገድ ላይ እንታገት ይኾን ወይስ ? በሰላም እንደርሳለን ? የሚለው ሃሳብ ሰቅዞ ይዞኛል። ልቤ በጭንቀት ተወጠረች።

እርሱስ በታገተበት መንገድ ድጋሜ መምጣት ምን የሚሉት ነው ? ተስፋ መቁረጥ ? አማራጭ ማጣት ወይስ ምንም አያመጡም የሚል ድፍረት ? በዚህ መንገድ ድጋሜ የመጣሁት የሀዘን ልብስ ስለለበስኩ ሲያዩኝ ልባቸው ይራራል በሚል እምነት ነው። ነገር ግን አሁንም ዋስትና የለኝም። ድጋሜ እንደማልታገት ግን ተስፋ አደርጋለሁ አለኝ።

አስተሳዝነው ዘንድ አቅም አጣሁ። ዝም ማለትን መረጥኩ። በክልሉ ውስጥ ባለው ግጭት ስንቶች እናታቸውን ሳያዩ ተነጠቁ ? ለአጋቾች መክፈል ያልቻሉ ስንቶች ተገደሉ? ስንቶች ሃብት ንብረታቸውን በታጣቂዎች ተዘረፉ? ቤት ይቁጠረው።

ወደ ራሴ ሃሳብ ተመለስኩኝ እኔስ በየብስ ጉዞ ማድረጌ ምን ፈተና ላይ ይጥለኝ ይኾን? እያልኩ ከውስጤ ጋር እየተወያየሁ ጉዞየን ቀጠልኩ። በአጋጣሚ በዕለቱ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከጎንደር ባሕር ዳር አሰሳ እያደረገ በመኾኑ በሰላም ባሕር ዳር መግባት ቻልን። ልጁን ተሰናብቸ ወደ ማረፊያየ አቀናሁ።

የመጣነውን መንገድ አሰብኩ። መቼ ነው ይህ እገታ፣ ዘረፋ እና ግድያ የሚቆመው? ሹፌሮች በነጻነት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡበት፤ ነጋዴዎች ሸቀጥ ከቦታ ቦታ በነጻነት የሚያጓጉዙበት፤ ልጅ እናቱን በሰላም የሚጠይቅበት፤ እናትም ከዚህ ጭንቀት የምትገላገለው መቼ ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎች አዕምሮየ ውስጥ ያለ እረፍት ተመላለሱ።

ያለ ሰላም ሁሉም ነገር ከንቱ ነው። ለሰላም በጋራ ካልሠራን ችግሩ ተራ እየጠበቀ በየቤታችን ይገባል። ሀዘኑም ለሁላችንም ይዳረሳል። ለሰላም በጋራ እንነሳ። በጋራ እንሥራ።

“ጊዜ ይፍታው” አይሠራም። ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት በመኾኑ ለሰላም እንትጋ። የንጹሐን መንገላታት እና መታገት ይብቃ። ልጅ ከወላጆቹ፣ ወላጆችም ከልጆቻቸው ጋር በሰላም ይገናኙ።
ሰላም ለሁሉም!

በያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሴቶች ወደ መሪነት እየመጡ ውጤታማ እየኾኑ ነው።
Next articleወጣቶች ሀገራዊ አመለካከት እንዲኖራቸው እየተሠራ ነው።