የእናትነት ጥበብ እና ደግነትን ለሰላም ግንባታም ማዋል ይገባል።

5

 

ባሕር ዳር: የካቲት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ “ለሰላም ዘብ እንቆማለን፤ የልማት አርበኛ እንኾናለን” በሚል መሪ መልዕክት ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ ሴቶች ጋር ውይይት አካሂዷል።

የከተማ አሥተዳድሩ ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ ሴቶች የውጭ ባዕዳዎችን እና የውስጥ ባንዳዎችን በማውገዝ እና በመከላከል አካባቢን ሰላም ማድረግ እንደሚገባቸው መክረዋል።

በሰላም እጦት የመጀመሪያ ተጎጅዎች ሴቶች ናቸው ያሉት መምሪያ ኀላፊዋ ለሰላም ከፍተኛ ሚና መጫዎት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

መምሪያ ኀላፊዋ በተለይም እናቶች እናታዊ ጥበብና ደግነታቸውን በመጠቀም ወደጫካ የወጡ ወጣቶች ለውይይት ዝግጁ እንዲኾኑ፣ ሰላምን እንዲመርጡ እና ከግጭት እንዲርቁ በመምከር እና መገሰጽ እንዳለባቸው መልእክት አስተላልፈዋል።
እናቶች ሰላም እንዲመጣ የማድረግ ትልቅ አቅም አላቸውም ነው ያሉት።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በተፈጠሩ ግጭቶች የደረሰውን ጉዳት ስላየን የክልሉ ሰላም ያሳስበናል ብለዋል። ግጭት ለሴቶች፣ ለአረጋዊያ እና ለሕጻናት አስከፊ ነውም ብለዋል።

ሰላም እንዲመጣ የእናትነት ሚናችንን እየተወጣን ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ ልጆቻችን ሰላምን እንዲመርጡ፣ ትምህርት እንዲማሩ፣ ወደ ግጭት እንዳይገቡ የመምከር እና የመገሰጽ ሥራ እየሠራን ነው ብለዋል። እናቶችን በማወያየት እና በመምከር ለሰላም እንዲሠሩ የማድረግ ሥራ በሰፊው መሠራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

እርስ በእርስ መገዳደል እንዲቆም እና ሰላም እንዲመጣ የእናትነት ድርሻችንን እንወጣለን ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleማንነት ድርድር አይደረግበትም።