
ባሕር ዳር: የካቲት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ የማሕጸን ጫፍ ካንሠር ምርመራ እና የግንዛቤ ፈጠራ መርሐ ግብር አካሂዷል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዝና ጌታቸው የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በተለየ ሁኔታ እየተከበረ ነው ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ሴቶች ስለማሕጸን በር ጫፍ ካንሰር ግንዛቤ እንዲኖራቸው እና እንዲመረመሩ የማድረግ ሥራ በተለያዩ ዞኖች መጀመሩንም ተናግረዋል። በሽታው ሳይታወቅ የሚያጠቃ በመኾኑ ሴቶች ራሳቸውን ማወቅ እና ጤናቸውን መጠበቅ አለባቸው ብለዋል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ ሴቶች ጤናቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ ከዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መርሐ ግብሮች ውስጥ አንድ አካል መኾኑን ተናግረዋል።
በዚህም በከተማ አሥተዳደሩ በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የማሕጸን በር ጫፍ ካንሰር ነጻ ምርመራ እየተካሄደ መኾኑን ገልጸዋል። ሁነቱ የሚቀጥል በመኾኑ ሴቶች ዕድሉን እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የሕክምና አገልግሎት ቡድን አሥተባባሪ ሲስተር መሠረት ባንትይገኝ የማሕጸን በር ጫፍ ካንሰር ሂውማን ፓፕሎማ ቫይረስ ከሚባል በሽታ አምጭ ሕዋስ የሚመጣ ነው ብለዋል።
በሽታው አይታከምም የሚባለው የተሳሳተ አመለካከት ነው ያሉት ባለሙያዋ ታክሞ መዳን የሚችል መኾኑንም ገልጸዋል። ሴቶች የሚዘጋጁ የምርመራ ፕሮግራሞችን መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በመርሐ ግብሩ ምርመራ ያደረጉ ሴቶችም የማሕጸን በር ጫፍ ካንሰር ን ተመርምሮ ጤናን ማወቅ የሚጠቅመው ለራስ ነው ብለዋል። በመርሐ ግብሩ ላይ ተመርመረው ራሳቸውን በማወቃቸውም ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
