ጦርነትን በማውገዝ ሰላም እንዲመጣ ማድረግ ከንግዱ ማኅበረሰብ ይጠበቃል።

11

 

ባሕር ዳር፡ የካቲት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር “ለሰላም ዘብ እንቆማለን፤ የልማት አርበኛ እንኾናለን” በሚል መሪ መልዕክት ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ተወያይቷል።

የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ነጻነት አጠቃ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት መኾኑን አንስተዋል። ሰላም ከሁሉም የቀደመ ነውም ብለዋል።

የነጋዴውም ማኅበረሰብ ሰላም እንጅ ጦርነት አይፈልግም ነው ያሉት። ከመንግሥት ጎን ኾነን ለሰላም እየሠራን ነውም ብለዋል።

በከተማዋ መንግሥት የሚያከናውናቸውን የልማት ተግባራት አድንቀዋል። ማኅበረሰብ ግብር በመክፈል እና የተለያዩ መዋጮዎችን በማድረግ ለመንግሥት ድጋፉን እያሳዬ መኾኑን ተናግረዋል።

መንግሥት የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በተለይም ነጋዴውን የሚያሳቅቁ አሠራሮችን እና ፈጻሚዎችን በማስተካከል፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን አጠናክሮ በማስቀጠል ወጣቶች ከግጭት እንዲወጡ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ሊያስቀጥል ይገባልም ብለዋል።

ለሰላም እና ለልማት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉም ተናግረዋል።

ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ ሙሉጌታ ውለታው ጦርነት እና ግጭት መቋጫቸው ድርድር መኾኑን ገልጸዋል። በግጭት ውስጥ የሚገኙ ኀይሎች የባሰ ውድመት ሳይደርስ ለድርድር እና ውይይት ቅድሚያ እንዲሰጡም አሳስበዋል። መንግሥት ውይይት እና ድርድር እንዲካሄድ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት ነው ያሉት።

የንግዱ ማኅበረሰብ ለታጣቂዎች ድጋፍ በማድረግ ጦርነትን ማስቀጠል እንደሌለበትም አንስተዋል። ጦርነትን በማውገዝ ሰላም እንዲመጣ ማድረግ ከንግዱ ማኅበረሰብ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።

የባሕርዳር ከተማ ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ አደራ ጋሼ ስለክልላዊ፣ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ለማኅበረሰቡ መረጃ መስጠት እና ማሠልጠን የውይይቱ ዓላማ መኾኑንም ተናግረዋል።

እንደማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ነጋዴዎች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር መጎዳታቸውን አንስተዋል። ነጋዴዎች እየታገቱ፣ እየተገደሉ እና እየተዘረፉ ነው ብለዋል። ነጋዴዎች መንግሥት ሰላምን ለማስከበር እያደረጋቸው የሚገኙ ተግባራትን መደገፍ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

ከተማ አሥተዳደሩ ነጋዴዎች ያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ እንደሚሠራ ተናግረዋል። ማኅበረሰቡም በተለያዩ የጸጥታ ስምሪት ውስጥ የሚገኘውን የጸጥታ ኀይል በተለያዬ አግባብ በመደገፍ ሰላም የማረጋገጥ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleብሎክቼይን – በዲጂታሉ ዓለም የማይናወጥ ዕምነትን መገንቢያ መሣሪያ