በአማራ ክልል ምን ያክል የመንገድ ፕሮጀክቶች ይገኛሉ ?

14

 

ባሕር ዳር፡ የካቲት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) መንገድ የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ እድገት የጀርባ አጥንት ነው።

በአማራ ክልል የመንገድ መሠረተ ልማት በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ አስታውቋል።

የአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር በዕቅድ ተይዘው በክልሉ የሚገኙት የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክቶች 61 መኾናቸውን ተናግረዋል። ከዚህ ውስጥ አሁን ላይ 49 የሚኾኑት የመንገድ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ ናቸው ብለዋል።

ቀሪ 12 የመንገድ ፕሮጀክቶች በተለያዩ ምክንያቶች ውላቸው እንደተቋረጠ አንስተዋል።

በሥራ ላይ ባሉ 49 የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክቶች ባለፋ ወራት 230 ኪሎ ሜትር ለመገንባት በዕቅድ ተይዞ እንደነበርም አስታውሰዋል። ከዚህ ውስጥ በ38 መንገድ ፕሮጀክቶች ላይ 84 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር እንደተሠራም ተናግረዋል። በክልሉ ባሉ የሪጅዮ ፖሊታንት ከተሞች ደግሞ 25 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር በክልሉ አቅም መገንባቱንም ገልጸዋል።

ከመንገድ ግንባታ በተጨማሪ የተለያየ ዓይነት እና መጠን ያላቸው 173 የኮንክሪት፣ የእግረኛ ተንጠልጣይ ድልድዮች እና ስትራክቸሮች እየተገነቡ መኾናቸውን አንስተዋል። ይህ መረጃ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስም 74 የሚኾኑት የግንባታ ሥራቸው መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ከመንገድ ግንባታ በተጨማሪ የተገነቡ መንገዶች ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጡ 19 ሺህ 772 ኪሎ ሜትር መንገድ በሁሉም ዘርፎች ለመጠገን ዕቅድ ተይዞ እንደነበረም ገልጸዋል። ባለፉት ስምንት ወራትም 12ሺህ 570 ነጥብ ኪሎ ሜትር የጥገና ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።

በሁሉም የመንገድ ግንባታ ዘርፎች ከ2 ሺህ 473 ኪሎ ሜትር መንገድ በላይ ለመገንባት በዕቅድ ተይዞ ነበር ብለዋል።ባለፋት ወራትም 1ሺህ 175 ኪሎ ሜትር መንገድ ተገንብቷል ነው ያሉት።

መንገዶቹ ከኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር በተጨማሪ በክልሉ መንግሥት መቀናጆ በጀት እና በኅብረተሰብ ተሳትፎ እየተገነቡ መኾናቸውን ጠቅሰዋል። ባለፉት ወራት 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ከኅብረተሰቡ በጥሬ ገንዘብ የማሰባሰብ እና ለማኅበረሰቡ የመንገድ ጥገና ሥራ የማዋል ሥራ መሠራቱንም አስታውሰዋል።

እስካሁን ከተገነባው መንገድ ውስጥ 1 ሺህ 66 ኪሎ ሜትር የሚኾነው የጠጠር መንገድ እንደኾነም አንስተዋል። ቀሪው 109 ነጥብ 12 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ መኾኑንም ገልጸዋል።

በሁሉም ዘርፎች 1ሺህ 12 የመንገድ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መኾናቸውን ተናግረዋል። ከዚህ ውስጥ 996 ፕሮጀክቶችን አጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል። መንገዶቹ በክልሉ መንግሥት፣ በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር እና በኅብረተሰብ ተሳትፎ እንደሚገነቡም አንስተዋል።

ውላቸው ተቋርጦ የቆሙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ለማስገባትም የጋራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቅሰዋል።

በተለያየ ጊዜ ቃል የተገቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ጥያቄዎች እና ፍላጎቶች እንዳሉ አንስተዋል። ፕሮጀክቶቹ በውሳኔ እና በበጀት አቅም ስለሚሠሩ እነዚህ መንገዶች በዚህ በጀት ዓመት የሚሠሩ አይደሉም ነው ያሉት። በቀጣይ ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የወሰን ማስከበር፣ የሥራ ተቋራጮች አቅም ማነስ፣ የነዳጅ አቅርቦት፣ የማሺነሪ ኪራይ፣ የኮንትራት አሥተዳደር ችግሮች እና የጸጥታ ሁኔታው የመንገድ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ እና በጀት እንዳይጠናቀቁ እንቅፋት ኾነዋል ብለዋል።

ከሦሥተኛ ወገን አንጻር ያለው ችግር ከሁሉም የሰፋ እንደኾነም አንስተዋል። ለዚህም የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ባለፉት ወራት ከ480 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ መክፈሉን ጠቅሰዋል።

6 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተከፈላቸው የልማት ተነሺዎች እንዳሉም ጠቁመዋል። ያም ኾኖ የክልሉ መንግሥት ለመንገድ ፕሮጀክቶች ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን አስታውቀዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰላም ጠንቅ እና የልማት ጎታች የኾኑ ኀይሎችን መታገል ይገባል።
Next articleቴክኖሎጂ የምርጫ ሂደቱን እያቀለለው ነው።