የጤና ሚኒስቴር ከዋና የኤሌክትሪክ መስመር ለራቁ የጤና ተቋማት የፀሐይ ኀይል አቅርቦት እያመቻቸ ነው።

2
አዲስ አበባ፡ የካቲት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኢትዮጵያ ከዋና የኤሌክትሪክ መስመር ርቀው የሚገኙ የጤና ተቋማት የሚያጋጥማቸውን የኀይል እጥረት ለመቅረፍ እና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስል በፀሐይ ኃይል አቅርቦት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾኑን አስታውቋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ዛሬ ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር ለክልሎች የሶላር ፓኔሎችን እና ሌሎች ግብዓቶችን ባስረከቡበት ወቅት መንግሥት የኀይል አቅርቦትን በተለያዩ አማራጮች ለማሟላት በትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
ዛሬ ለክልሎች በፀሐይ ኀይል የሚሠሩ ሶላሮች፤ ለክትባት እና ለመድኃኒት ማከማቻ የሚውሉ ማቀዝቀዣዎች፣ ሞተሮች እና ሌሎች ተያያዥ መሣሪያዎች መሰጠቱን ነው የጠቆሙት።
በተያዘው ዓመት ከ600 በላይ የጤና ተቋማትን ተጠቃሚ ለማድረግ የታቀደ ሲኾን ዛሬ ብቻ ለ380 ጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች የሚውሉ ቁሳቁሶች መከፋፈላቸውን ገልጸዋል።
ለዚህ ፕሮጀክት የቀረቡት የሶላር ፓኔሎች ግምታቸው ከ4 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደኾነም አስረድተዋል። በቀጣይም ተጨማሪ 700 ፓኔሎች ተሰራጭተው የጤና ተቋማቱን አገልግሎት ለማጠናከር ዝግጅት መጠናቀቁም ተገልጿል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማኅበራዊ፣ ባሕል እና የስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ወርቀሰሙ ማሞ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ የሚገኙ የጤና ተቋማትን ችግሮች ለመፍታት የተጀመረው ሥራ የሚበረታታ መኾኑን ጠቅሰዋል። ሥራው ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።
በዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር አቡበከር ካምፓ የክትባቶችን ደኅንነት ለመጠበቅ እና አስተማማኝ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የኀይል አቅርቦት ወሳኝ መኾኑን አስምረውበታል። ዩኒሴፍም ለኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ቃል ገብተዋል።
ዘጋቢ፦ ተመስገን ዳረጎት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!!
Previous article“ዐይኔን የገበርኩት ለሀገሬ በመኾኑ አይቆጨኝም” የካራማራው ጀግና