
ባሕር ዳር፡ የካቲት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዘመናትን የተሻገረው፤ ግን ደግሞ ዘመን አይሽሬ የኾነው የካራማራ ድል ደማቅ ታሪክ እነኾ 48 ዓመታትን አስቆጠረ።
የዛሬው ባለታሪካችን የካራማራ ነገር ሲነሳ አብሮ የሚመዘዝ ቁርኝት ያላቸው ናቸው። እኒህ ባለታሪክ ለሚወዷት ሀገራቸው ሲባል ውድ ነገራቸውን ሁሉ ሰጥተዋል። ላባቸውን፣ ደማቸውን እና በምንም ሊተካ የማይችለውን ዐይናቸውን ሁሉ ያለስስት ለሀገራቸው ለግሰዋል።
ባለታሪካችን አስር አለቃ አዝመራው ወርቅነህ ደስታ ይባላሉ። የ68 ዓመት ሽማግሌ ናቸው። ምሥራቅ ጎጃም ዞን ድጎ ጽዮን ማርያም ነው ተወልደው ያደጉት። በ1969 ዓ.ም በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ጎረቤት አገሮች መካከል በተፈጠረው ያልተገባ ጦርነት ላይ እንቢ ለሀገሬ ብለው ተሳትፈዋል። በዘመኑም የሀገር ፍቅር ስሜቱ ከፍ ያለ ነበር ሲሉም ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ትውስታቸውን አጋርተዋል።
ኢትዮጵያውያን ሁሌም መደፈርን አይወዱም ነው ያሉት። በትግልም የማልታማ ነኝ ሲሉ የጀግንነታቸውን ልክ አዋዝተው ነግረውናል። ሀገራችን ምን ያህል ሰፊ እንደኾነች የተረዳሁት በኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት በተሳተፍኩበት የለጋ ዕድሜየ ነው ብለዋል።
የጦርነት በጎ ባይኖረውም ይላሉ ባለታሪካችን ከሶማሊያ ጋር የነበረው ውጊያ የትጥቅ አለመመጣጠን ስለነበረ ከባድ ነበር ብለዋል። የድሉ ምስጢር ግን ቁርጠኝነት እና ከልብ የመነጨ የሀገር ፍቅር ነው ባይ ናቸው።
በዚያ አስቸጋሪ ቀን መመኪያችን የኾነው የአየር ኀይላችን ሢሠራው የነበረው ጀብድ እጅን ከአፍ ላይ የሚያስጭን ነበር ይላሉ። የኢትዮጵያውያን መስዋዕትነትን በመቀነስ ረገድ ትልቅ ታሪክ የሠራ የአየር ኀይል እንደነበርም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ሲቪሉ ማኅበረሰብም በሀገር ፍቅር ስሜት ሲያደርግ የነበረው እገዛ ታሪክ አይሽሬ እንደነበር አስታውሰዋል።
ዶሎ ላይ እና ካራማራ ላይ የነበረው የጨበጣ ውጊያ ዛሬም ዐይኔ ላይ ይታየኛል ይላሉ አስር አለቃ አዝመራው። በልበ ሙሉነት እየተዋደቁ ባሉበት የገናሌ ውጊያ ላይ የተከበበ ጦር ለማስለቀቅ በሚደረግ ጥረት በፈንጅ ፍንዳታ ዐይናቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸውም ነግረውናል።
ከብዙ መስዋዕትነት በኋላ ካራ ማራ ላይ የኢትዮጵያ ወታደር ሰንደቅዓላማውን ከፍ አድርጎ ሲያውለበልብ በሁሉም ጓደኞቻችን ዘንድ የነበረው ደስታ ወደር አልነበረውም ነው ያሉት።
ብዙ ጓደኞቸ በነበረው ጦርነት የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ እኔ ደግሞ ሁለቱ ዐይኔ በውጊያ ወቅት ጠፍቷል የሚሉት አስር አለቃ አዝመራው ተዋድቀንም ቢኾን ሀገሪቱ ነጻ በመውጣቷ ለደስታዬ ቃላት የለኝም ይላሉ።
“ዐይኔን የገበርኩት ለሀገሬ በመኾኑ ዛሬም ድረስ አይቆጨኝም” ነው ያሉት። ለሀገር ዋጋ መክፈል ያለ እና የነበር መኾኑን የዛሬው ትውልድ ሊገነዘብ ይገባልም ብለዋል። ዛሬም እንደ ትናንቱ ትውልዱ ዝቅ ሲል ላቡን፣ ከፍ ሲል ደግሞ ደሙን ገብሮ ሀገሩን መጠበቅ አለበት ባይ ናቸው።
ዛሬም በግፍ የተወሰደው የባሕር በራችን ከመሞቴ በፊት ለእናቴ ኢትዮጵያ ተመልሶ እንዳየው እመኛለሁ ብለዋል። አደራውም ለዚህ ትውልድ ይሁን ነው ያሉት።
“ቀይ ባሕር ደማችን አሁንም ቀይናት ጀግኖች በደማቸው እስካሁን ያቆዩት” ሲሉም በውጊያ ወቅት ጓደኛቸው ይዘፍንላቸው የነበረን ዜማ እና ግጥም አስታውሰዋል።
ባለታሪካችን በካራማራ ጦርነት በጻፉ ደማቅ ታሪክም ከሀገሪቱ የወቅቱ መሪ ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም እጅ የክብር ሜዳሊያ ተበርክቶላቸዋል።
በመጨረሻም ይላሉ አስር አለቃ አዝመራው ይች ሀገር እንደዋዛ ከዚህ አልደረሰችም ብለዋል። ወታደርነት ተወዳጅ ሥራ ነው፤ ዛሬም እንደገና ብፈጠር ሀገሬን ወታደር ኾኘ ባገለገልኩ ነበር ነው ያሉት።
ለሀገር ባለውለታዎች መንግሥትም ኾነ ሕዝቡ ዋጋ ሊሰጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አንዳርጌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!!
