በእናት ያስጨከነው የሀገር ፍቅር

10
ባሕር ዳር፡ የካቲት 26/2018ዓ.ም(አሚኮ) ኢትዮጵያ ተከብራ የኖረችው ቀጣይም የምትኖረው ለስጋ ብቻ ሳይኾን ለነፍሳቸው ባልሰሰቱ ልጆቿ አጥንት እና ደም ነው።
የካራማራ ጀግኖች ደግሞ ለእናት ሀገራቸው አጥንት እና ደማቸውን ሳይሰስቱ ከሰጡት መካከል በጉልህ የሚጠቀሱ ናቸው። ይህንን እስከ መስዋትነት የደረሰ የሀገር ፍቅርም ኢትዮጵያውያን ለረጅም ዘመናት በቃላዊ ግጥም እያወሱት ቀጥለዋል።
እንሂድ? የት?
ካራማራ “ምን ልንሰራ?”
“ጀግና ቆጠራ” “እርሱ እኮ የለም ምኑን እንቁጠር?”
“አጥንቱን” ምን ሲል ሞቶ ነው? “እናቱን!”
እያሉ ለሀገር የሚከፈል የመስዋዕትነት ታሪክ ለተተኪው ትውልድ እየነገሩ ዛሬ ላይ ደርሰዋል።
ካራማራ ፍጹም የሀገር ፍቅር የነገሰበት፣ አንድነት የጎለበተበት፣ ብርታት ለሽንፈት እጅ ያልሰጠበት፣ አለመግባባት እና ቅራኔ ወደ ጎን የተተወበት እና የኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክ የተገመደበት ነው። የዚያድባሬን ጦር ለመመከት እና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከሁሉም ጉዳይ በላይ ሀገርን ያስበለጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ቀላል አይደለም።
ከእነዚህ ኢትዮጵያውያን መካከል በደራሲ መቅደስ አበበ በተጻፈው የካራማራ ግራሮች የተሰኘው የታሪክ መጽሐፍ ላይ የሰፈረው ወታደር ጋሻየ አንዱ ነው። ታሪኩ ላይ እንደተገለጸው ወታደር ጋሻየ በልቡ የሚስላት እና በዓይኑ የሚያያት ሀገሩ የተለያየ ቁመና ላይ በመኾናቸው ቁጭት እና ንዴት ከንግግሩ መሀል የማይጠፉ ለሀገሩ ተጨናቂ ነው።
በዚህ ስሜት ላይ እያለ በ1969 ዓ.ም ኢትዮጵያን ለመውረር ራሷን በበቂ ሁኔታ ስታደርጅ የቆየቸው ሶማሊያ ድንበር አልፋ ገባች፡፡ “ሀገር ተወራለች እና ተነስ ታጠቅ” የሚል ዜና ከደርግ ሊቀመንበር ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም መተላለፋን እንደሰማ ለዘመቻ ቀዳሚ ተሰላፊ ኾነ። እርሱ ብቻ ሳይኾን በዕድሜ ትንሹንም ትልቁንም ኢትዮጵያዊ አስቆጣ፡፡
ወታደር ጋሻየ በወቅቱ በነበሩ ሀገር መሪ ግለሰቦች እና መንግሥት ላይ ቅሬታ ቢኖረውም ቅሬታውን ወደጎን ትቶ የእሱን ድጋፍ ብቻ የሚጠባበቁ ቤተሰቦቹ ላይ ጨክኖ ነበር የታጠቅ ምልምል ጣቢያ ላይ የተገኘው።
በወቅቱ የነበረውን የእርስ በርስ አለመግባባት ሲገልጽም ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል ያሉት ነገር ነው የደረሰብን አለ። ሶማሊያ የዋዛ አይደለችም በንጉሡ ጊዜ ያንን በመሰለ ዱላ ከተመለሰች በኋላ ቀን፣ ሰዓት አስልታ እና ቆጥራ የውስጥ ድክመቶችን በመጠቀም ነው እኮ ለወረራ የተሰናዳቸው ነበር ያለው። ዛሬም ቢኾን የውስጥ ድክመቶቻችን ሊጠቀሙ የሚሞክሩ እንደሚኖሩ ይህ ታሪክ አስረጂ ነው።
ወታደር ጋሻየ በዕድሜ ለገፉ እናቱ ብቸኛ ልጅ ነው፡፡ ጎጆ ማቆም፣ ልጅ ማሳደግ የሚቻለው ሀገር ስትኖር ነው ብሎ ጎጆ ምስረታውን ሰርዟል፡፡
ለትምህርት እንኳ ሂዶ የእናቱ ናፍቆት አላስችል ብሎት ትምህርቱን ባቋረጠላት በሚሳሳላት እናቱ ጨክኖ ሀገሩን አስቀድሟል፡፡
ለምን ሲባልም ሀገር ኾነችብኝ ነበር ያለው፡፡ የሀገር ፍቅር አይቶ እና አውርቶ በማይጠግባት፣ እናት እና አባት እንኳ በሌላት ነፍሰጡር እጮኛው አስጨክኖታል። ምን ዓይነት የሀገር ፍቅር ነው?
ከእልህ አስጨራሽ ትግል በኋላም በየካቲት ወር 1970 ዓ.ም ጦርነቱ በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት የመጠናቀቅ ዜና ተሰማ፤ ደስታ እና ፌሽታ ኾነ። ወታደር ጋሻየ ግን በዕድሜ ከገፉ ከደካማ እናቱ በላይ በቁጭት ለተንሰፈሰፈላት እናት ሀገሩ የልቡን አድርሶ በጀግንነት እና በከብር ተሰውቷል፡፡
ይህ የሞት ዜና ብቸኛ ልጇ ለኾነች እናቱ ከባድ ነው። ልጁን አቅፋ በጉጉት ለምትጠብቅ እና ፍቅሯ በጅምር ለቀረች የፍቅር አጋር ሕመሙ በቃል የሚገለጽ አይደለም። ለሀገሩም እንደዛው፤ ነገር ግን ሀገር ስትኖር ሁሉም እንደሚኖር በታሪኩ አስተማረ።
አሚኮ ዲጅታል ሚዲያ ኢትዮጵያውያን ከዚህ አይነት የድል ታሪክ ምን ልንማር እንደሚገባ ያነጋገራቸው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መመህር እና ተመራማሪ ገረመው እስከዚያ (ዶ.ር) አሁን ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን ከካራማራ እና ሌሎች ድሎች አንድነትን፣ መተሳሰብን፣ ሉዓላዊነትን ማስጠበቅን፣ ነጻነትን እና ልዩ ልዩ ጉዳዮችን ልንማርበት ይገባል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያውያን አባቶች መራራ ትግል፣ በጎ አመለካከት፣ ቁርጠኝነት፣ ኅብረት የተገኘውን ድል በሀገር ግንባታ፣ ልማት፣ እድገት እና የወደፊት ራዕይ ማንጸባረቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ለመጭው ትውልድ የማንነት ነጻነትን እናወርሳለን” አቶ አሸተ ደምለው
Next article“ዐይኔን የገበርኩት ለሀገሬ በመኾኑ አይቆጨኝም” የካራማራው ጀግና