“ለመጭው ትውልድ የማንነት ነጻነትን እናወርሳለን” አቶ አሸተ ደምለው

4
ሁመራ፡ የካቲት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እንዲሳተፍ ምርጫ ቦርድ የሰጠውን መመሪያ ተከትሎ በሁመራ ከተማ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
በሰልፉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ለመጭው ትውልድ የማንነት ነጻነትን እናወርሳለን ብለዋል።
የዞኑ አሥተዳደር በሕግ አግባብ ሕዝቡን እያሥተዳደረ መኾኑን ገልጸዋል። አሥተዳደሩ እና ሕዝቡ ለነጻነቱና ለማንነቱ ዛሬም እንደትናንትናው ዓላማው የጸና ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ፣ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ እንዲሳተፍ ላስተላለፈው ውሳኔ ምስጋናቸውን ያቀረቡት አሥተዳዳሪው በምርጫው መሳተፍ ሕገ መንግሥታዊ መብት መኾኑንም አንስተዋል።
ይሄንን እድል ለመንጠቅ ለሚሞክሩ አካላትን ሁልጊዜም ዝግጁ በመኾን መታገል ይገባል ነው ያሉት። በአንድ እጃችን ለልማት፣ በሌላኛው እጃችን ደግሞ ለነጻነታችን እየታገልን ነው ብለዋል።
የዞኑ ሕዝብ ጥያቄና ትግል በአዲስ ምዕራፍ ላይ መኾኑንም ጠቁመዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ አማራ ነው፤ ፍጹም የኢትዮጵናዊነት መንፈስን ታጥቆም ሰላሙን እየጠበቀ የሚያለማ ነው ብለዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ በኾነ መልኩ እናካሂዳለን ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ለፈጠረን እንጂ ለፈተነን አንንበረከክም ነው ያሉት።
የሰቲት ሁመራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ እንኳየነህ ሙሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕግ መሰረት ለፍትሕ ወዳዱ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እንዲሳተፍ የወሰነውን ፍትሐዊ ውሳኔ እናደንቃለን ብለዋል።
ይህ ውሳኔ በሚዛናዊነት የተሰጠ መኾኑን ያነሱት ከንቲባው የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የዞኑ ሕዝብ በአማራ ክልል ምክር ቤት የሚወከልበትን ምርጫ እንዲያካሂድ ማመቻቸት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ሰልፈኞቹም ትናንትም ዛሬም አማራ ነን የሚሉ መልእክቶችን አስተጋብተዋል። ምርጫ ቦርድ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እንዲሳተፉ የሰጣቸውን እድል ለመጠቀም በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
አማራዊ ማንነታቸውን ለማስከበር ከዞኑ አሥተዳደር ጋር በጽናት እንደሚቆሙም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ አምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሕዝቡ የመምረጥ መብት በእጁ ነው።
Next articleበእናት ያስጨከነው የሀገር ፍቅር