ምንጩ ያልታወቀ ሃብት ማለት ምን ማለት ነው ?

10
ባሕር ዳር፡ የካቲት 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎ምንጩ ያልታወቀ ሃብት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ሁለንተናዊ ጉዳት አያደረሰ በመኾኑ፣ የሕገወጥ ድርጊትን የጥቅም ምንጭነት ለመከላከል፣ ተበታትነው የሚገኙ ተዛማጅ ሕጎችን በአንድ አጠቃልሎ በማውጣት ለአፈጻጸም ምቹ ለማድረግ፣ የሕጉን ተፈጻሚነት ለማስፋት እና በወንጀል የተገኙ ንብረቶች የሕግ ማዕቀፍን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ የኢፌዴሪ የንብረት ማስመለስ አዋጅ 1364/2017 ወጥቷል፡፡
ምንጩ ያልታወቀ ንብረት እንዴት እና እሰከምን ድረስ ይገለጽ ይኾን? በሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 መሰረት ኀላፊነት ያለባቸው አካላት ምንጩ ያልታወቀ ንብረት እንደተጠበቀ ኾኖ፣ ከሕጋዊ ገቢው የማይመጣጠን፣ ምክንታዊ የወንጀል ጥርጣሬ በኖረ ጊዜ እና የንብረቱን ምክንያት ለፍርድ ቤት ያላስረዳ ሰው ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ተብሎ ይወረሳል፡፡
ምንጩ ያልታወቀ ነው ብሎ በጠረጠረው ንብረት ላይ እንዲያስረዳ በዐቃቤ ሕግ የተጠየቀ ሰው በሁለት ወር ውስጥ ቀርቦ ማስረዳት እንዳለበት አዋጁ ያስቀምጣል፡፡
ማስረጃ እንዲያቀርብ የተጠየቀ ሰው በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ማስረጃ ካላቀረበ ዐቃቤ ሕግ በፍርድ ቤት ክስ ይመሠርታል፡፡
አዋጁ ተፈጻሚ መኾን ከመጀመሩ አሥር ዓመት በፊት የተገኘ፣ ምንጩ ያልታወቀ እና ግምቱ ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ የኾነ ንብረትን ለማስመለስ ክስ እንደሚመሠረት ነው አዋጁ የሚያስቀምጠው፡፡
ከግለሰቦች እና ከተቋማት ጥቆማ በመጣ ጊዜም ምርመራ ሊጀመር እንደሚችልም ያትታል፡፡ ማንኛውም ሰው ወይም ተቋም ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ለሚመረምር አካል ማስረጃ የማቅረብ ግዴታም ይኖርበታል፡፡
መርማሪው አካል ያገኘውን መረጃ ለሥራው ካላስፈለገው፣ በፍርድ ቤት ካልታዘዘ እና ከፍትሕ ሚኒስትሩ ፈቃድ ካላገኘ በስተቀር መረጃውን ለሌላ አካል አሳልፎ መስጠት አይችልም፡፡
ክስ የተመሠረተበት ንብረት እስከ አንድ ዓመት የሚቆይ እግድ ወይም መያዣ ትዕዛዝ ሊተላለፍበትም ይችላል፡፡ ንብረቱ የተያዘበት ወይም የታገደበት ሰውም የይነሳልኝ ጥያቄ ሊያቀርብ እንደሚችል ተቀምጧል፡፡
በዚህ አዋጅ የቤተሰብ አባላት የዕለት መተዳደሪያ እና ቁሳቁስ፣ ለተከሳሹ እና ለቤተሰቡ የአንድ ዓመት ስንቅ እንዳይታገድ ትዕዛዝ ሊሰጥ እንደሚችል ያትታል፡፡
በዚህ አዋጅ በወንጀል ድርጊት ንብረት ስለመገኘቱ እና ለሌላ ሰው ስለማስገኘቱ ከተረጋገጠ የንብረት ማስመለሱ እና መውረሱ ተፈጻሚ ይኾናል፡፡
ንብረት የማስመለስ ክስ በተመሠረተበት ሰው ላይ በፍርድ ሂደት አለያም ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ አዲስ የተገኘ ንብረት ካለ ዐቃቢ ሕግ አዲስ የንብረት ማስወረስ ማመልከቻ ሊያቀርብ እንደሚችል አስቀምጧል፡፡
በፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ ቅሬታ ያለው ወገን ይግባኙን ለበላይ ፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚችል አዋጁ ያትታል፡፡ ማንኛውም ሰው በወንጀል ድርጊት ጥቅም ያገኘ፣ ለሌላም ያስገኘ ወይም በሌላ ሰው ጥቅም ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደኾነ በዐቃቤ ሕግ አመልካችነት እና ክርክር በፍርድ ቤት እንዲወረስ ሊበየን ይችላል፡፡
በአዋጁ በጥፋተኝነት ያልተመሠረተ የንብረት መውረስ ማመልከቻ የሚቀርበው ከሚከተሉት ቢያንስ አንዱ ሲሟላ ነው፡፡
👉በወንጀል ድርጊት የተጠረጠረው ሰው ሲጠፋ፣ ሲሞት ወይም ሳይታወቅ ሲቀር።
👉የተገኘው ማስረጃ ለወንጀል ሥነ ሥርዓቱ ተቀባይነት ከሌለው።
👉በይርጋ ምክንያት የወንጀል ጥፋተኝነት ማሰጠት ሳይቻል ሲቀር።
👉ተከሳሹ ከቀረበበት የወንጀል ክስ ነጻ ሲባል ወይም ክሱ ሲቋረጥለት።
👉ከጥፋተኝነቱ ጋር የሚገናኝ ኾኖ በሦሥተኛ ወገን ይዞታ ሥር ጭምር ያለ ንብረት ሲኾን።
👉ተጠርጣሪው ያለመከሰስ መብት ያለው ሲኾን እና በመሰል ምክንያቶች ነው፡፡ በንብረቱ ላይ መብት አለኝ በሚል ሦስተኛ ወገን ጠያቂነት የተያዘ ንብረት አሥተዳዳሪ እንዲሾም ሲጠየቅ ፍርድ ቤቱ የንብረት አሥተዳደር እንዲሾም ሊያዝዝ ይችላል ሲልም አዋጁ ያስቀምጣል፡፡
የተወረሰ ንብረትን ስለመጠቀም አዋጁ ሲገልጽ የሚወረሰው ገንዘብ ወይም ንብረት ለተጎጂው ይመለሳል። ሚኒስቴሩ ለዚህ ዓላማ ሲባል ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሊተባበር እንደሚችልም ነው አዋጁ የሚገልጸው፡፡
የሚወረስ ንብረትን ጥቆማ ለሰጠ ሰው ንብረቱ የተወረሰ እንደኾነ ማበረታቻ እንደሚሰጠው አዋጁ ያትታል፡፡ በአዋጁ ተጎጂዎች በወንጀል የተገኘው ንብረት የግለሰብ ወይም የተቋም ከኾነ የተገኘው ንብረት እንዲመለስ ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት ማስረጃ እንዲያቀርብ ተጠይቆ ያልተባበረ ሰው ከመገደዱ በተጨማሪ እስከ ሦሥት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ሊቀጣ ይችላል፡፡
ማስረጃ አለመስጠት፣ መደበቅ፣ ምስጢራዊነቱን አለመጠበቅ እና ሌሎች የሕጉ ተቃርኖ ድርጊቶች በአዋጁ በእሥራት ያስቀጣሉ፡፡
ዘጋቢ፦ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!!
Previous article“አንድ በሚያደርገን ላይ ሥንሠራ ሀገር አንድ ትኾናለች፣ ሰላም ትኾናለች፣ ትበጽጋለች” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article“ጥያቄያችን ለእውነትና ለፍትሕ ነው” የወልቃይት ጠገዴ እና ሰቲት ሁመራ ዞን ነዋሪዎች