ግብርናው ከበሬ ትክሻ ወደ ትራክተር እርሻ እየተሸጋገረ ነው።

3

 

ባሕር ዳር: የካቲት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ግብርናውን ለማዘመን እና ምርታማነትን ለማሳደግ የእርሻ ሜካናይዜሽን ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮም ከበሬ ትክሻ ያልወረደውን ባሕላዊ የአስተራረስ ዘዴ ከሰው እና እንስሳት ጉልበት አውጥቶ በዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ ለመተካት እየሠራ ነው።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው
ግብርናውን ከኋላ ቀር የበሬ እርሻ በማላቀቅ፣ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሠራሮችን በማስተዋወቅ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል ።

ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ (ሜካናይዜሽን ) ምርታማነትን እንደሚጨምር ተናግረዋል። ጊዜን እና የሰው ኃይል ጉልበትን ከመቆጠብ ባለፈም የእርሻ ሥራን ጥራት በማሻሻል የምርት ብክነትን ለመቀነስ ጉልህ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት። አንድ ትራክተር በቀን ከአምስት ሄክታር በላይ ያርሳል ብለዋል።

በክልሉ 2 ሺህ 726 ትራክቶች እንደሚገኙም ገልጸዋል። ባለፉት ስድስት ወራትም 619 ትራክተር ፣ 10 ኮምባይነር፣ ከ555 በለይ የበቆሎ መፈልፈያ፣ 612 ትሬሸር እና ከ6 ሺህ በላይ ሞተር ፓንፕ ለአርሶ አደሮች መሠራጨቱን ተናግረዋል። ይህም የአርሶ አደሮችን የግብርና ሜካናይዜሽን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሚናው የጎላ እንደኾነ ገልጸዋል።

የአርሶ አደሮች የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እያደገ መምጣቱን አንስተዋል። ምዕራብ ጎንደር፣ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ፣ አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ምሥራቅ ጎጃም እና ሰሜን ሼዋ ዞኖች የተሻለ የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ልምድ ያለቸው አካባቢዎች መኾናቸውንም ጠቅሰዋል ።

ግብርናው ከበሬ ትክሻ ወደ ትራክተር እርሻ እየተሸጋገር መኾኑን ገልጸዋል።

በክልሉ 1ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እርሻ እየለማ ይገኛል ያሉት ምክትል ኀላፊው ከበሬ እርሻ ሥራ በመውጣት በዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን በመጠቀም የምግብ ለአላዊነትን ለማስከበር እየተሠራ እንደሚገኝም አመላክተዋል።

አርሶ አደር ቤዛ ዓለሙ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሶሊበን ወረዳ ነዋሪ ናቸው። ዘመናዊ የአስተራረስ ዜዴን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩ ሁለት ዓመታትን አስቆጥረዋል። ዘንድሮም ሁለት ሄክታር መሬት በትራክተር አሳርሰዋል።

በትራክተር ማረስ የሰብል ተባይን ይቀንሳል፣ ማሳውን በቀላሉ ማለስለስ ይቻላል፤ ምርታማነትን ይጨምራል ነው ያሉት። የአርሶ አደሮችን እና የበሬዎችን ጉልበት ይቀንሳልም ብለዋል። ጊዜንም ይቆጥባል ነው ያሉት። ከአንድ የእርሻ ማሳ የሚያገኙት ምርት በግማሽ እጥፍ ይጨምራል ብለዋል።

ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ በመከተላቸው የኑሩ ደረጃቸውን ማሻሻል መቻላቸውንም ነግረውናል።

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሁሉም መስክ ጠንካራ ለውጥ ለማምጣት ጠንካራ የሕዝብ ግንኙነት ያስፈልጋል።
Next articleዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መከበር በሴቶች እኩልነት እና ነጻነት ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል።