
ባሕር ዳር፡ የካቲት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት “ለሰላም ዘብ እንቆማለን፤ የልማት አርበኛ እንኾናለን” በሚል መሪ መልዕክት ከከተማ፣ ከክፍለ ከተማ እና ከቀበሌ መሪዎች ጋር መክሯል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሁሴን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከተማ አሥተዳድሩ በሰላም፣ በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል።
በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ሥራ እየተነጋገርን በመሄዳችን ለውጥ አምጥተናል ነው ያሉት።
ከተማ አሥተዳደሩ እና ሕዝቡ በሚፈለገው ልክ ለውጥ ለማምጣት አሁንም በርካታ ሥራዎች ይቀራሉ ብለዋል። በሁሉም መስክ ጠንካራ ለውጥ ለማምጣት ጠንካራ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ እና ውይይት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
ጠላቶች የሀገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ እየሠሩ መኾናቸውን ለሕዝብ በማስረዳት መግባባት እና የውጭ ስጋትን እንዲከላከል ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ከዚህም በላይ ሰላምን ለማጽናት፣ ልማትን ለማረጋገጥ እና የመልካም አሥተዳደር ለውጥ ለማምጣት አሁንም ተግባብቶ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ዛሬ የተጀመረው የሕዝብ ግንኙነት እና የፖለቲካ ሥራም እስከታች የሚወርድ መኾኑን አመላክተዋል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ለሰላም ዘብ መቆም እና ለልማት አርበኛ መኾን ከሁሉም መሪዎች እና ማኅበረሰብ የሚጠበቅ መኾኑን ተናግረዋል። ይህን ግንዛቤ ለማስረጽም እስከ ታች መድረኮች ይካሄዳሉ ብለዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የልማት፣ የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እና ለፕሮጀክቶች አፈጻጸም የፖለቲካ ሥራ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ለዚህም ጠንካራ የፖለቲካ እና የሕዝብ ግንኙነት ሥራ በመሥራት ከማኅበረሰቡ ጋር መግባባት ይጠይቃል ነው ያሉት።
የውይይቱ ተሳታፊ የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ክህሎት መምሪያ ኀላፊ ዘመነ አሰፋ ከተማዋ ሰላማዊ ናት፤ በዚህም ከፍተኛ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ውይይቱ ልማት እና ሰላሙን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ መኾኑንም ተናግረዋል። በሰላም እና በልማቱ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደኾነም ጠቅሰዋል።
የአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ሥራ አሥኪያጅ ኤልያስ አሳዬ የልማት፣ የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች በቅንጅት እየተሠሩ እንደኾነ ጠቁመዋል።
የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል እና የሚፈጠሩ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እየሠራን ነው ብለዋል።
ስለውጫዊ ጫናዎች እና ውስጣዊ የጽንፈኝነት አስተሳሰብ ማኅበረሰቡን በማወያየት እና ግንዛቤ በመፍጠር የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ከግብ ለማድረስ እንደሚሠሩም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!!
