
ፍኖተ ሰላም፡ የካቲት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) መምህርት ብርቱካን ጌታሁን በፍኖተሰላም ከተማ 01 አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት ናቸው። የተማሪዎች ምገባ መርሐግብር ሳይመገቡ ወደ ትምህርት ቤት በሚመጡ ተማሪዎች ላይ የነበረውን የመማር ማስተማር ችግሮች የሚቀርፍ መኾኑን ተናግረዋል።
በተለይም የተማሪዎችን ከትምህርት የመቅረት ምጣኔ በማሻሻል በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲኾኑ እንደሚያግዝ ገልጸዋል። የምገባ መርሐግብሩን አጠናክሮ በማስቀጠል የነገ ትውልድ ተረካቢ ታዳጊዎች ላይ መሥራት እንደሚገባም መምህርቷ ጠቁመዋል።
የፍኖተሰላም 01 አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ተመስገን መኮነን ሕጻናት ላይ መሥራት የነገ ትውልድ ተረካቢዎች ላይ መሠረት መጣል መኾኑን ተናግረዋል።
ለዚህም በትምህርት ቤቶች ላይ እየተከናወነ ያለው የተማሪዎች ምገባ ወሳኝ ነው ብለዋል። በትምህርት ቤቱ 314 ተማሪዎች የምገባ ተጠቃሚ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
በፍኖተሰላም ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት ተግባር ተኮር የጎልማሶች ባለሙያ እና የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርተ ቤት ተጠሪ ከሀሊው ቢተው በከተማ አሥተዳደሩ በሰባት ትምህርት ቤቶች ላይ የምገባ መርሐግብር ለማካሄድ እየተሠራ ነው ብለዋል።
እስካሁንም በሁለት ትምህርት ቤቶች ላይ የምገባ መርሐግብር እየተካሄደ መኾኑን አንስተዋል። በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ላይም ከ2ሺህ በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለሙያ ፍስሐ ደምለው
በምዕራብ ጎጃም ዞን 15 ሺህ 279 ተማሪዎችን የምገባ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ከክልል፣ ከወረዳዎች እና ከኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከ46 ሚሊዮን በላይ ብር በጀት የተማሪ ምገባ ለማካሄድ እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ለዚህም የሚያስፈልጉ ግብዓቶች መቅረባቸውን አንስተዋል።
እስካሁንም በ19 ትምህርት ቤቶች ላይ 9ሺህ 650 ተማሪዎች የምገባ መርሐግብሩ ተጠቃሚ መኾናቸውም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!!
