
ባሕር ዳር፡ የካቲት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰፊ በኾነ የእንስሳት ቁጥር እና ብዝኀ ሕይወት የታደለ ነው። ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እና ለውጭ ገበያ የሚውል ከፍተኛ የሥጋ፣ የወተት፣ የማር እና ሌሎች የእንስሳት ውጤቶችን የማምረት አቅም አለው።
የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ጋሻው ሙጨ (ዶ.ር) የእንስሳት ሃብት በምግብ ራስን ለመቻል፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የውጭ ምንዛሬን ለማምጣት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል። በመንግሥት በኩል በተሠጠው ትኩረትም ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተነቃቃ መምጣቱን ገልጸዋል።
ይህንን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በክልሉ የእንስሳት ሀብት የላቀ ውጤት ለማምጣት በልዩ ትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል። በዝርያ ማሻሻል፣ በመኖ አቅርቦት፣ በቴክኖሎጅ አጠቃቀም፣ በእንስሳት ጤና አጠባበቅ እና የዘርፉን መሠረተ ልማት በማሟላት ላይ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን አብራርተዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግ በሁሉም ዞኖች ያሉትን ጸጋዎች እና ምቹ ሁኔታዎችን በመለየት በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ላይ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
የመኖ ችግርን ለመፍታት የተሻሻሉ የመኖ ዘሮችን ለተጠቃሚው ለማቅረብ በጥናት ተለይቶ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል። በክልሉ ከ42 በላይ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። ከመጠን፣ ከጥራት እና ከዋጋ አንጻር በቂ ባለመኾናቸው ክፍተቱን ለመሙላት ከባለሃብቶች እና ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ለዘርፉ የመሠረተ ልማት ከማሟላት አንጻርም የመሬት እና የፋይናንስ አቅርቦትን ለማሻሻል ከባንኮች እና ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አመላክተዋል። በቴክኖሎጅ አቅርቦት ላይም በስፋት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በዶሮ እርባታ ዘርፍ ያጋጥም የነበረውን የአንድ ቀን ጫጩት አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ የዶሮ ብዜት ማዕከላትን እያስፋፉ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ዘርፉ ለበርካታ ወጣቶችም የሥራ ዕድል እየፈጠረ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ለአብነትም በዚህ ዓመት ከ90 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለም አንስተዋል።
ባለሀብቶችም ክልሉ ያለውን ጸጋ እና ምቹ ሁኔታ በመገንዘብ በእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!!
