
ባሕር ዳር፡ የካቲት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ21018/19 የምርት ዘመን ለመኸር እርሻ የግብርና ግብዓት ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እያከናወነ መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው በበጀት ዓመቱ 8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ከወደብ ወደ ክልሉ እየተጓጓዘ መኾኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ በዩኔየኖች 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ይገኛል፤ ይህም ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች ጥቅም ላይ እንደሚውልም አስረድተዋል።
በክልሉ 230ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ ታቅዶ እስካሁን 131ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር የማባዛት እና የመሠብሠብ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። ግብዓትን ከማቅረብ ባለፈ ለአርሶ አደሮች ተደራሽ እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል።
ለ2018/19 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ስጋት እንደማይኾንም ተናግረዋል። የአርሶ አደሮችን ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ቴክኖሎጂን ተደራሽ በማድረግ በዘመናዊ መንገድ እንዲያመርቱ እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል።
የመኸር እርሻ በአብዛኛው አካባቢ በተለይም በምዕራብ አማራ መጀመሩን ገልጸዋል። በቀጣይ በሁሉም አካባቢ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመኸር እርሻ ከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በሰብል ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። አርሶ አደሮች ማሳቸውን በማለስለስ ለዘር ማዘጋጀት፣ ግብዓት በወቅቱ መውሰድ የግብርና ባለሙያ የሚሰጣቸውን ምክረ ሀሳብ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የደቡብ አቸፈር ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ማግኘት ጥላሁን የእርሻ ሥራ እየጀመሩ መኾኑን ጠቁመዋል። ለእርሻ ሥራ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ከማዘጋጀት ባለፈ ለግብዓት መግዣ የሚኾን ገንዘብ ማዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።
አራት ሄክታር የእርሻ መሬት አለኝ የሚሉት አርሶ አደሩ ባለፈው ዓመት ከ2 ሄክታር መሬቱ ላይ 35 ኩንታል ዳጉሳ እና 60 ኩንታል የበቆሎ ምርት ማግኘታቸውን ነግረውናል።
አርሶ አደር ማግኘት ጥላሁን እንደተናገሩት ባለፈው ዓመት የምርት ዘመን ቀድመው እርሻ በመጀመራቸው የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ቀድሞ የእርሻ ሥራ መጀመር የሰብል ተባይን ለመቀነስ እና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
ሌሎች አርሶ አደሮችም ወደ እርሻ ሥራ ቀድመው መግባት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
