“ከአባቶች ጥንካሬን በመውሰድ የአይቻልም መንፈስን ሰብረናል” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

6

ባሕር ዳር፡ የካቲት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገርን ከወራሪ ለማዳን፤ ያልተደፈረ ነጻነትን እና ክብርን ለማስጠበቅ፤ ለሉዓላዊነት የደም ዋጋ ለመክፈል ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተባብረዋል።

ኢትዮጵያውያን ለጥቁሮች ሰብዓዊ መብት መከበር ፈር ቀዳጅ በመኾን በዓድዋ ድል አሸናፊነትን አረጋግጠዋል። ለበርካታ አፍሪካውያን የማንቂያ ደውልም ኾነዋል።

በአማራ ክልል ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ፣ ነጻ እና ተአማኒ ምርጫ እንዲከናወን በአማራ ክልል የወጣቶች ክንፍ አሥተባባሪነት ለወጣቶች ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል። የማጠቃለያ መርኀ ግብርም ዛሬ ተከናውኗል።

በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ስለ ዓድዋ ድል መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ዓድዋ የአንድነት መገለጫ የኢትዮጵያውያን ኩራት፤ የአፍሪካ ተምሳሌት መኾኑን ገልጸዋል።

በዓድዋ ኢትዮጵያውያን በአንድነት እና በመተባበር መረጃ በማቀበል፤ ስንቅ በማዘጋጀት እና ጦር ሜዳ በመዋጋት በአንድነት ድል ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ነጻነቷን በማስከበር ለአፍሪካ ሕዝብ ነጻነት ምሳሌ መኾን መቻሏንም አንስተዋል። ከዓድዋ ጀግንነትን በመማር የአይበገሬነት መንፈስን በማስቀጠል ኢትዮጵያውያን በአንድነት ዳግማዊ ዓድዋ የሕዳሴ ግድብን እውን ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በአንድነት ተግዳሮቶችን አልፈናል ነው ያሉት። ከአባቶች ጥንካሬን በመውሰድ የአይቻልም መንፈስን ሰብረናልም ብለዋል።

ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ሰጭነት ተቀይረናል ነው ያሉት። መንግሥት ኢትዮጵያ በአፍሪካ መሪ እንድትኾን የሚያስችላትን ተግባር እያከናወነ መኾኑንም ተናግረዋል።

የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የኒኩለር ኀይል ማበልጸጊያ፣ የነዳጅ ምርት፣ የወርቅ ፋብሪካ እና ሌሎች የጉባ ብሥራት ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ ለማበልጸግ የሚሠሩ ተግባራት ናቸው ብለዋል።

ወጣቶች ከዓድዋ ጀግንነትን በመማር የዘመኑ የልማት ጀግና መኾን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።በቴክኖሎጅው ዘርፍ ወጣቶች እያከናወኑ ያሉትን ተግባራት አጠናክረው እንዲቀጥሉም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲከናወን የወጣቶች ሚና የጎላ ነው።